በስምንተኛ ክፍል የጥያቄ እና መልስ ውድድር አሸነፈ

የአቡነ ጎርጎርዮስ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ፍቅር በሱፍቃድ በተሳተፈባቸው የጥያቄ እና መልስ ውድድር ላይ ከፍተኛ ብልጫን በማስመዝገብ አሸናፊ ሆነ፡፡
በቃሊቲ ክፍለ ከተማ በወረዳ ስምንት ከሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጋር በተደረገ የቀለም ትምህርት የጥያቄ እና መልስ ውድድር ላይ አንደኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የሰርተፍኬት ተሸላሚ መሆን ሲችል ለትምህርት ቤቱም የዋንጫ ሽልማት ማምጣት ችሏል፡፡
ተማሪ ፍቅር የወረዳውን ውድድር በስኬት በማጠናቀቁ በክፍለ ከተማ ከአስራ ሶስት ወረዳዎች ከተውጣጡ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ጋር በተካሄደው ውድድር አንደኛ መውጣት ችሏል፡፡ በእውቀት እና በሥነ ምግባር የታነጸው ይህ ተማሪ ክፍለ ከተማውን በመወከል በከተማ ደረጃ በተካሄደው ውድድር ላይ ተሳትፎ የተጠየቃቸውን ሁሉንም ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ በመመለስ አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡
በዚህም ተማሪ ፍቅር በወረዳ፣ በክፍለ ከተማ እና በከተማ ደረጃ ባደረጋቸው ውድድሮች የተጠየቃቸውን ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ በመመለስ እና ተፎካካሪ በመሆን ለመጨረሻው ዙር ለአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ላይ መቅረብ ችሏል፡፡
በጥያቄ እና መልስ ሂደት ውስጥ በማለፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ 5 ተማሪዎች በተወዳደሩበት በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በተካሄደው የመጨረሻው ዙር ውድድር ላይ ከፍተኛ ፉክክር በማድረግ በመለያ ጥያቄ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ እና ከአዲስ አበባ ከተማ ት/ቢሮ ኃለፊ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡
ተማሪ ፍቅር በተጓዘባቸው የውድድር ሂደቶች እጅግ አመርቂ የሚባል ውጤትን በማስመዝገብ የዘለቀ ሲሆን ውድድሩ በጣም አስተማሪ እንደሆነ እና እንደዚህ አይነት ውድድር ላይ ተሳትፎ እንደማያቅ በማንሳት ትልቅ ልምድ የወሰድኩበት ነው ብሏል፡፡ እንዲሁም በርትቶ ማጥናት ከተቻለ ሁሉም ነገር ላይ መድረስ ይቻላል በማለት ብርቱ ዝግጅት በማድረግ ሀገራችንን እና ትምህርት ቤታችንን እናስጠራ ሲል መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
የቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ገንዘቤ ገለታ ይህን አይነት ውጤት በተማሪው መመዝገቡ ነገ ሌሎች ተማሪዎችም በጥያቄ እና መልስ ውድድር ብቻ ሳይሆን በሥነ ጽሁፍ እና በፈጠራ ሥራ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ተወዳዳሪ እና የተሻለ ሆኖ መገኘት እንዲችሉ ትልቅ መነቃቃትን መፍጠር ያስቻለ ነው ብለዋል፡፡
መላው የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ በተመዘገው ውጤት ትልቅ አስተዋጽዎ አበርክቷል፡፡ በተገኘው ውጤት እና በትልቅ መድረክ ትምህርት ቤቱን ማስጠራት በመቻሉም ደስታውን በመግለጽ ለተማሪው ሽልማት አበርክቶለታል፡፡