በአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የገፅ ለገፅ ትምህርትን ለመጀመር ዝግጅት ተጠናቋል

የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች በ2012 ዓ.ም በአለምአቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ /ኮቪድ 19/ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የገጽ ለገጽ ትምህርት ለማስጀመር ዝግጅቶቻቸውን አጠናቀው ተማሪዎችን ለመቀበል በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ወቅት በትምህርት ሚኒስቴር እና በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ትምህርት ቢሮ የወጡትን ወረርሽኙን ለመከላከል የተቀመጡ መመዘኛዎችን በሁሉም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶቻችን እንዲሟሉ ተደርጓል፡፡

የግንዛቤ ስራዎችን ለማከናወን እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ስጋት እንዳይኖርባቸው ለማድረግ የተቀናጀ ስራ በመሰራት ላይ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት አግባብነት ያላቸው የስልጠና ማኑዋሎችና የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ የትግበራ ህገ ደንቦች ተዘጋጅተው በወጥ መርሀ ግብሮች በመታገዝ ለመምህራን፣ ለረዳት መምህራን፣ ለሞግዚቶች፣ ለጽዳትና ውበት ሰራተኞች፣ ለጥበቃ ሰራተኞች እና ለአጠቃላይ የአስተዳደር ሰራተኞች ስልጠናዎች ተሰጥተው ሙሉ ዝግጅቱ በተቀናጀ መንገድ በመተግበር ላይ ነው፡፡

በየትምህርት ቤቶቹ በሚገኙ የወላጅ ተማሪ መምህራን ህብረት /ወተመህ/ ተሳትፎ በመታገዝ ለተማሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎች ጭምር የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብሮች ተከናውነዋል፡፡ ከወተመህ ጋር ከሚከናወኑ ውይይቶች በተጨማሪ ወላጆችና ተማሪዎች ስለበሽታው ያላቸውን ግንዛቤ አስቀድሞ ከፍ ለማድረግ የተለያዩ የማህበረሰብ ሚዲያዎችን በመጠቀም ማንዋሎችንና ህገደንቦችን የማስተዋወቅ ስራ በሰፊው በመከናወን ላይ ነው፡፡

በያዝነው የዝግጅት ምእራፍም ከግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት በተጨማሪ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችና በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ ግብአቶች በተገቢው መንገድ እንዲሟሉ መጠነ ሰፊ ተግባራት በየደረጃው በተዋቀሩ ግብረሃይሎች በመታገዝ እየተሰሩ የሚገኙ ሲሆኑ አብዛኛዎቹ ተግባራት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል፡፡

በተጨማሪም በተለያዩ እውቅና ፍቃድ ሰጪዎች የተረጋገጠ ፍቃድ ባላቸው ድርጅቶች የታገዘ የጽዳትና የፀረ ተህዋስያን ኬሚካል ርጭት ተደርጓል፡፡ ርጭቱም በአንድ ወቅት ብቻ ተከናውኖ የሚቋረጥ ባለመሆኑ ድግግሞሽ ባለው መንገድ እቅድን መሰረት አድርጎ መከናወን እንዲችል የውል ስምምነት ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት መመሪያው ላይ የተካተቱ መስፈርቶች ማሟላትን በተመለከተ ግምገማ ለማድረግና ፍቃድ ለመስጠት በተዋቀሩ የትምህርት ቢሮና የሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ባለሙያዎች አማከኝነት በተደረገ ግምገማ ትምህርት ቤቶቻችን አብዛኛውን መስፈርቶች በማሟላታቸው የትምህርት ዘመኑን ትምህርት በተቀመጠለት መርሀግብር መጀመር እንዲቻል ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በ2012 ዓ.ም ክልላዊና ብሄራዊ ፈተናን የሚሰጡ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል 5 ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶቻችን ተማሪዎች በትምህርት ቢሮ በተዘጋጀው መርሀግብር መሰረት ከጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተቀመጡትን መስፈርቶች በማሟላት የመማር ማስተማር ስራዎችን በጥሩ ሁኔታ ጀምረዋል፡፡ በአሁኑ ሰኣት መማር ማስተማሩን በመስጠት ላይ የሚገኙ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶቻችን አዋሬ፣ ወይራ፣ ሲኤምሲ፣ ለቡና ባህርዳር ናቸው፡፡

በተከናወኑ የትግበራ ዳሰሳዎች መሰረት የትምህርት አሰጣጡና ተማሪዎቹንም ሆነ አጠቃላይ ሰራተኞቹን ከበሽታው ለመከላከል የሚደረገው ጥረት አስተማማኝ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በተለይም ለ8ኛ ክፍሎች የ7ኛ ክፍልንና የ8ኛ ክፍልን ትምህርቶች መሰረት ባደረገ መልኩ የተዘጋጀውን ወቅታዊ መርሃ ትምህርት በመተግበር ተማሪዎች በስናልቦናም ጭምር ዝግጁ እንዲሆኑ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በተመሳሳይም የ12 ክፍል የትምህርት ክንውንም በተጠናና በተቀናጀ መንገድ በመሰጠት ላይ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ የሚያስችሉና መማር ማስተማሩን የሚያጎለብቱ መሰረታዊ ግብአቶች በበቂና በአስተማማኝ ሁኔታ ለሁሉም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶቻችን እንዲዳረሱ ተደርጓል፡፡ ምንም እንኳን ወቅቱ በትምህርት ቤቶች የኢኮኖሚ አቅም ላይ ያደረሳቸው ተጽኖዎች ከፍተኛ ቢሆንም ተጽኖዎቹን በመቋቋም እና ለትምህርት ጥራት ትኩረት በመስጠት አስፈላጊ የትምህርት ግብአቶችን በበቂ ሁኔታ የማሟላት ተግባራቱ ተጠናቀዋል፡፡ ከሰው ሀይል አንጻርም አስፈላጊ የሆኑና ብቃትን መሰረት ያደረጉ የመምህራንና አጠቃላይ ሌሎች ሰራተኞች ቅጥር ተከናውኖ ስልጠናዎች ጭምር ተደራሽ መሆን የቻሉ ሲሆን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የዝግጅት ምእራፍ ተግባራትን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ተችሏል፡፡