‹‹በዓለም በብዙ ዘርፎች ላይ የሚሠራ የኤሮስፔስ ተቋም እንዲኖረኝ እሻላሁ››

‹‹በዓለም በብዙ ዘርፎች ላይ የሚሠራ የኤሮስፔስ ተቋም እንዲኖረኝ እሻላሁ››

የቀድሞ የአቡነ ጎርጎርዮስ ተማሪ የነበረው ትንሣዔ አለማየሁ በቅርቡ የአፍሪካ ሕዋ ኢንዱስትሪ አሥር ከ30 ዓመት በታች ያሉ ወጣቶች ተብለው ከተመረጡት መካከል መካተት ችሏል።
ይህ ይፋ ከሆነ ከቀናት በኋላ ደግም የስፔስ ጄኔሬሽን አድቫይዘሪ ካውንስል የአፍሪካ አስተባባሪ ሆኖ መመረጥ ችሏል።
ትንሣዔ አለማየሁ 23 ዓመቱ ነው። ከአሥሩ አፍሪካዊያን መካከል በዕድሜ ትናንሾቹ እሱና የዚምባብዌው ታፋድዝዋ ባንጋ ናቸው። ስለ ሕዋ ሳይንስ አውርቶ አይጠግብም። ‹‹በሕዋ ሳይንስ ገደብ የሚባል ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር ይቻላል›› ይላል።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የአምስተኛ ዓመት የሜካኒካል ምህንድስና ተማሪ ነው። በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የመቀለ ቅርንጫፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆኖም ይሠራል።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ጄኔሬሽን 2000 የተሰኘ ትምህርት ቤት ነው የተከታተለው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት ተምሯል። አጠቃላይ አሁን የደረሰበትን ቢቢሲ አማርኛ በቃለ መጠይቅ ያቀረበውን ከተወሰነ ማስተካከያ ጋር እንዲህ ቀርቧል፡፡
እንዴት ወደ ሕዋ ሳይንስ?
የሕዋ ሳይንስ ቀልቤን ይገዛው የጀመረው በታሪክ አማካኝነት ነው ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
«ልክ ወደ ‹‹ሃይ ስኩል›› ልገባ አካባቢ ነው ፍላጎቴ እየጨመረ የመጣው። የታሪክ መፃሕፍትን፤ የብራና ጽሑፎችን ለመዳሰስ ስሞክር ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ነገር በተወሰነ መልኩ ማየት ቻልኩ። ባሕሪዬ ሆኖ ብዙ ያልተዳሰሱ ሐሳቦችን ማየት እወዳለሁ።»
‹‹ማርስ ላይ ሕይወት ነበረ?›› ለሚለው ጥያቄ መልስ ሊገኝ ነው ሳተላይት ኢንተርኔት ምንድን ነው?
በሳተላይቶች ዙሪያ ሰባት አስደናቂ እውነታዎች ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቋ ለምን ይጠቅማታል?
«የኢትዮጵያ ስም በታሪክ፣ በሕክምና እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ሊነሳ ይችላል። በሕዋ ዘርፍ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው ብቅ ብቅ ማለት የጀመረው። የብራና መጻሕፍት ላይ የድሮ አባቶች በጊዜው በነበራቸው አረዳድ የሕዋ ሳይንስን የተረዱበት መንገድ ያስደንቀኝ ነበር።»
«እንደ ሌላው በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተነሳ ሳይሆን የታሪክ ጥናት ነው ወደዚህ መስመር ያመጣኝ ብዬ አስባለሁ።»
ነገር ግን በሕዋ ሳይንስ የበለጠ እንድሳብ ያደረጉት የአቡነ ጎርጎርዮስ የሁለተኛ ደረጃ የፊዚክስ መምህሩ እንደሆኑ ይናገራል።
ከ30 ዓመት በታች ያሉ የሕዋ ሳይንስ ባለተስፋዎች መካከል ትንሣዔ የዘንድሮው የአፍሪካ ሕዋ ኢንዱስትሪ ከ30 ዓመት በታች ያሉ አሥር ወጣት አፍሪካዊያን የሚለውን እውቅና ያገኘው በሌሎች አካላት በዕጩነት ቀርቦ ነው።
ትንሣዔ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ሊካተት ይገባል ሲሉ ስሙን ለስፔስ ኢን አፍሪካ ተቋም ያስገቡት አንድ የሞሮኮ ተቋምና የስፔስ ጄኔሬሽን አድቫይዘሪ ካውንስል ሊቀመንበር እንደሆነ ያወሳል።
ከዚያ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ዳኞች የቀረበላቸውን መረጃ አመሳክረው ከአሥር አፍሪካዊያን መካከል ሊሆን ይገባል ሲሉ እውቅና እንደሰጡት ያስረዳል። ምንም እንኳ በመቀለ ዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ ዓመት የሜካኒካል ምህንድስና ተማሪ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ምክንያት የትምህርት ሁኔታው ተንጠልጥሎ እንዳለ ያስረዳል።
«እኔ እንደውም አጋጣሚ ሆኖ ‹‹ለኢንተርኒሺፕ›› የምወጣበት ድርጅት አዲስ አበባ ሆኖ እዚህ [አዲስ አበባ] ስለመጣሁ ነው እንጂ ብዙ ተማሪዎች መቀለ እንደነበሩ አውቃለሁ። በቅርቡ ነው ነዋሪነታቸው ከትግራይ ክልል ውጭ የሆኑ ተማሪዎች የመጡት።»
«ያው የኢንተርኒሺፕ ፕሬዘንቴሽን ሁላ አላቀረብኩም። እዚህ እንደመጣሁ ነው ሁኔታዎች የተቀየሩት። ያው አለን። ተንጠልጥለን።»
የትኛውን የሕዋ ኤጀንሲ ማየት ትመኛለህ? ትንሣዔ በሕይወትህ አንድ የሕዋ ኤጀንሲ ብቻ ነው ማየት የምትችለው ብትባል የቱን ትመርጣለህ?
«እባክህ ሦስት ይሁልንኝ»
እሺ ልፈቅድልህ «ያው የአሜሪካው ናሳ አለ። በጣም ረዥም ጊዜ በዘርፉ የተሰማራ እንደመሆኑ። ከዚያ ደግሞ ኢሳ አለ  ‹‹የአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲ። ከዚያ በመቀጠል የጃፓኑ ጃክሳ ይመጣል።»
ሩሲያና ቻይናን በምርጫህ ታካትታለህ ብዬ ገምቼ ነበር?
«እርግጥ ነው ቻይና በጣም ትልቅ አቅም አላት። ነገር ግን እስከአሁን ሁሉም ሰው ሊያየው የሚችለው ዓይነት ሥራ አልሠሩም ወይም ዓይን ውስጥ አልገቡም። የሩሲያ ሕዋ ኤጀንሲም እንደዚሁ ትልቅ ሚና አለው ግን እኔ ብዙም አይደለሁም።»
ትንሣዔ ወደ ቱርክ አቅንቶ በአንካራ ያለውን ‹‹ኦብዘርቫቶሪ›› መጎብኘቱን ይናገራል። ነገር ግን የሁልጊዜ ህልሙ ግን እነዚህን ሦስት ማዕከላት መጎብኘት እንደሆነ ይናገራል።
«በጣም በስፋት ወደ ስፔስኤክስ አደላለሁ።»
ትንሣዔ ለምን የዘመኑ የሕዋ ሳይንስ የግል ድርጅት ፈርጥ እየተባለ ወደሚባለው ኢላን ማስክ ሊያደላ ቻለ?
«ኢላን መስክ ለሕዋ ያለው አስተሳሰብና ጄፍ ቤዞስ ያለው አተያይ በጣም የተለያየ ነው ብዬ አምናለሁ። ጄፍ የቢዝነስ ሰው ነው። የሆነ ነገር ሸጬ አትርፌ አመጣለሁ ብሎ የሚያስብ ሰው ነው። በሌላ በኩል ኢላን የቢዝነስ ዘርፉን ብቻ ያስባል ብዬ አላስብም። እርግጥ ነው ስኬታም የሆነው ጠንካራ የቢዝነስ ሰው ስለሆነ ነው። ነገር ግን ቢዝነሱን የሚዘውረው ሳይንሱ ነው ብሎ ያምናል።»
ትንሣዔ፤ የቤዞስ የሕዋ ሳይንስ ድርጅት የሆነው ብሉ ኦሪጂንና በቅርቡ ቨርጂን ጋላክቲክ በተሰኘው ድርጅቱ አማካኝነት ወደ ሕዋ ደርሶ የተመለሰው ሪቻርድ ብራንሰን ከኢላን በተቃራኒ ‘ስፔስ ቱሪዝም ላይ ያተኩራሉ የሚል እምነት አለው።
ኢትዮጵያና የሕዋ ሳይንስ
«ማንም ሰው ወደኋላ እንደቀረ የሚታወቀው መካፈል አለብኝ ብሎ የሚያስበው ጥቅም ሲቀርበት ነው። ለምሳሌ እነ ኢላን እየሠሩ ያሉት ‘ስታርሊንክ’ ማንም ሰው እንደፈለገ የማያጠፋው ኢንተርኔት እንዲኖር ያደርጋል።»
ትንሣዔ ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር የዳታ ፉክክር ነው ይላል። ኢትዮጵያ በሕዋ ሳይንስ መስክ የሚቸግራት ነገር የለም ሲል ያክላል።
«የሚይዘን ነገር ምጣኔ ሃብቱና ፖለቲካው ነው። የሕዋ ሳይንስ በራሱ ራሱን የቻለ ትልቅ ፖለቲካ አለው። ኢትዮጵያ የራሷን ሳተላይት ለማስወንጨፍ የምታወጣው ወጪና ያደጉ የሚባሉ ሃገራት የሚያወጡት ወጪ አይገናኝም። ነገር ግን ኢትዮጵያ ያለችበት ቦታ ሳተላይት ለማስወንጨፍ በጣም አመቺ ቦታ ነው።»
«ብዙ ሰዎች እውነት ኢትዮጵያ ሳተላይት ያስፈልጋታል? ይላሉ። ነገር ግን ቀን በቀን የምንጠቀመው ኤቲኤም በለው አሊያም የሳተላይት ቴሌቪዥን ሥርጭት እንዲሁም ሌሎች መስኮችን ስታይ ያስፈልገናል አያስፈልገንም የሚለው ክርክር ውስጥ መግባት አልነበረብንም። በሳተላይት አማካኝነት ለምንጠቀመው ነገር የምንከፍለውን ገንዘብ ማስቀረት እንችላለን።»
ትንሣዔ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሕዋ ሳይንስ ትምህርትም ሆነ አገልግሎት ጥቅም የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች ቀናቸው ያለፈባቸው ናቸው ይላል።
«ነገር ግን ትላልቆቹ የሕዋ ኤጀንሲዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂ እያመረቱ ስለሆነ እኛ እንደ አዲስ ማምረት አይጠበቅብንም።»
ወደ ዓለም አቀፉ የሕዋ ጣቢያ የመሄድ ዕቅድ አለህ?
«እርግጥ ነው የከፍታ ፍርሃት ያለበት ሰው ካልሆነ በቀር ወደላይ ሄዶ ማየት የማይመኝ ሰው አለ ብዬ አላስብም። ነገር ግን በቅርቡ ከነ ቤዞስ አሊያ ሪቻርድ ጋር እንደሄዱት ሰዎች ሕዋ ላይ ደርሶ መምጣት ዋጋ አለው ብዬ አላስብም» የትንሳዔ ምላሽ ነው።
«ምክንያቱም ደርሶ መምጣት ደርሶ መምጣት ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ገንዘብ ካለህ ደርሰህ መምጣት ትችላለህ ማለት ነው። 240 ሺህ ዶላር ካለህ ትችላለህ።»
«ዓለም አቀፉ የሕዋ ጣቢያ በጣም ትልቅ ቤተ ሙከራ ነው። ፍላጎቱ እንዳለኝ የሚካድ አይደለም። ነገር ግን እኔ ወደዚያ መሄድ የምመኘው ሄጄ የምሠራው ነገር ሲኖር ነው።»
የወደፊት ዕቅድህ ምንድን ነው?
«እኔ ቅድሚያ የምሰጠው ትምህርቴን አጠናክሮ መቀጠል ነው። ምክንያቱም እውቀት መር የሆነ ነገር ይዘን መንቀሳቀስ መቻል አለብን። እንግዲህ ፈጣሪ በፈቀደ ጊዜ ድግሪዬን እጨርሳለሁ። ከዚያ ወደ ማስተርስ። ነጥቡ ግን ድግሪ መያዝ አይደለም። በሕዋ ዘርፍ የራሴን እንድወጣ ያደርገኛል የምለውን ዕውቀት ይዞ መውጣት ነው።»
ትንሣዔ ዕቅዱን ከጨብጥኩ በኋላ ወደ ሕዋ ኢንዱስትሪ መቀላቀል እንደሚፈልግ ይናገራል።
«አስትሮናት የመሆኑ ሐሳቡ ስላለኝ በተለያየ ዘርፍ ዕውቀት እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ዘርፉ በጣም ሰፊ ስለሆነ ጠቅላላ ዕውቀት ይፈልጋል። ልማዳዊውም ኢ-ልማዳዊውን ትምህርትን መቅሰም እፈልጋለሁ።»
«በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም በብዙ ዘርፎች ላይ የሚሠራ የኤሮስፔስ ተቋም እንዲኖረኝ እሻላሁ።»
ምንጭ፦ ቢቢሲ ኒውስ አማርኛ

የአክሲዮን ማህበራችንን ድህረ ገፅ https://esdros.com/e/ እና በፌስቡክ ገፃችን https://www.facebook.com/Esdros-Construction-Trade-and-Industry-SC-282021025628947 በመከታተል ወቅታዊ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡