አክስዮን ማኅበሩ ሥልጠና ሰጠ

ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ ለሥራ አመራሮች፣ ለርዕሰ መምህራን እና ለምክትል ርዕሰ መምህራን በኢትዮጵያ ሆቴል ሥልጠና ሰጠ፡፡
የአመለካካት ለውጥን ለማሳደግ እና የደንበኛ አገልግሎት አሰጣጥን የተሻለ ማድረግ ያስችል ዘንድ “Attitude Skills for Success at Work in Life” እና “ customer service in an organization” የደንበኞች አገልግሎት በድርጅት ውስጥ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተሰጥቷል፡፡
ሥልጠናው በ2015ዓ.ም ከተያዘ እቅድ መካከል ሲገኝ የአክስዮን ማኅበሩ የሰው ሀብት አስተዳደር መምሪያ፣ ከኒው አፍሪካ ኮንሰልተንሲ ፈርም እና ከዳይሬክተሮች ቦርድ ጋር በመተባር ያዘጋጀው ሲሆን የሥልጠናው ዋና ግብ ተሳታፊዎቹ ተገቢ የሆነ የአመለካከት ዕውቀትን እና ክህሎትን እንዲጨብጡ በማድረግ በሥራቸው እና በአኗኗራቸው ዘይቤ ለውጥ እንዲያመጡ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
በተጨማሪም የድርጅቱን የአመራር ብቃት ይበልጥ ለማሳደግ ፣ የሰራተኞችን አመለካከት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ፣ በትምህርት ጥራት ፣ሥነ ምግባር እንዲሁም ውጤታማ የሥራ አፈጻጸም ለማምጣት ታስቦ ሥልጠናው ተሰጥቷል፡፡
በዕለቱ የአክስዮን ማኅበሩ የፋይናንስ እና አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አንተነህ ፈለቀ የመክፈቻ ንግግር በማድረግ የሥልጠናውን መርሃ ግብር ያስጀመሩ ሲሆን በንግግራቸውም ድርጅቱ በ2014ዓ.ም ለ642 ሰራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች በ13 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሥልጠናዎችን መስጠት እንደቻለ በመጥቀስ በተያዘው በ2015 በጀት ዓመትም የሰራተኛውን እና የሥራ ኃላፊዎችን አቅም ከማጎልበት አንጻር 22 ሥልጠናዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች 1200 ለሚሆኑ ሰራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ለመስጠት እቅድ እንደተያዘ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ የአመራር ብቃት በማሳደግ የደንበኞችን እርካታ ከፍ ለማድረግ ያግዝ ዘንድ ሥልጠናውን እንዳዘጋጀ የጠቀሱት አቶ አንተነህ ሰልጣኞች በሚኖራቸው ቆይታም በንቃት እንዲከታተሉ እና ፍሬያማ ጊዜን ማሳለፍ እንዲችሉ በማሳሰብ ንግግራቸውን አጠቃለዋል፡፡
አሁን ያለውን አመለካከት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ያስችል ዘንድ “Attitude Skills for Success at Work in Life” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሥልጠና የሰጡት የኒው አፍሪካ ኮንሰልተንሲ ፈርም መስራች፣ ዋና ስራ አስፈጻሚ እና በሥራ አመራር ዘርፍ የተመሰከረላቸው አማካሪ የሆኑት አቶ አሸናፊ አበራ ሲሆኑ በሥልጠናቸውም አመለካከት በየዕለቱ በህይወታችን የምናየው እና በሚገጥሙን ነገሮች የምንፈጥረው እይታ ነው ብለዋል፡፡ በሥልጠናቸው ጨምረውም አንድ ነገር በራሱ መጥፎም ጥሩም እንዳልሆነ ነገር ግን የምንቀበልበት መንገድ መጥፎ ወይም ጥሩ እንደሚያደርገው በማንሳት ወደ አዎንታዊ አመለካካት ወይም አስተሳሰብ የመውሰድን ትልቅነት አጉልተው ማሳየት ችለዋል፡፡
ሌላው የአክስዮን ማኅበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል የሆኑት ወ/ሮ እንዬ ቢምር በደንበኛ አገልግሎት እና ተግባቦት ላይ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን የተግባቦት መንገዳችን ከወላጆች እና ከተማሪዎች፣ ከድርጅቱ አመራሮች እና ሰራተኞች እንዲሁም ከሌሎች ደንበኞች ጋር ምን መምሰል ይኖርበታል? ለሚነሱ ጉዳዮችስ መፍትሄ ከመስጠት አንጻር በምን መንገድ ተግባቦታችን መቃኘት ይኖርበታል? የሚለውን አጽኖት በመስጠት አሰልጥነዋል፡፡ በተጨማሪም የድርጅቱ ደንበኞች የሆኑትን ወላጆች የአገልግሎት እርካታን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስፈልጉ ክህሎቶችን ለተሰሳታፊዎች በሚገባ አስርጸዋል፡፡
በሥልጠናው ተሳታፊ ከሆኑት መካከል የወይራ ቅድመ መደበኛ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት የሆኑት ወ/ሮ ማህሌት ኤፍሬም ሲገኙበት በሥልጠናው ትልቅ የህይወት ልምድ እንደተማሩ በመጥቀስ በእያንዳንዱ የሥልጠና ቆይታቸው ያላቸውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማሰብ እና በማነጻጸር ትልቅ ትምህርት እንዳገኙበት ተናግረዋል፡፡
አቶ የአብስራ አለማየሁ የእግዚአብሔር አብ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሲሆኑ በሥልጠናው ያላቸውን አስተያየት አመለካከትን እንዴት መስራት እና መቀየር እንደምችል በደንብ ማየት የቻልኩበት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በአጠቃላይ ከዚህ ሥልጠና በኋላ ወደየቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶቻቸው ሲመለሱ በተመሳሳይ መልኩ ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እና አጋር አካላት የወሰዱትን ሥልጠና በማውረድ ድርጅቱ ያቀዳቸውን ስልታዊ እና ዓመታዊ ግቦች እንደሚያሳኩ ቃል የገቡ ሲሆን ድርጅቱም በዚሁ አግባብ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
በመጨረሻም በሥልጠናው ላይ በመገኘት የመዝጊያ ንግግር የአክስዮን ማኅበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ዋና ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ታደሰ አሰፋ ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም በ2015ዓ.ም ከደንበኞች አገልግሎት ጋር ያለንን ግንኙነት ከፍ የምናደርግበት እና ይሄንኑ በተግባር የምናሳይበት እንዲሁም ቃል የምንገባበት መሆን መቻል አለበት ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ያገኛችሁትን ሥልጠና ወደ ዕቅድ በማውረድ ለመስራት ዝግጁ መሆን ተገቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ብሎም አስተሳሰብ ላይ የሚኖራችሁን አመለካከት አጎልብታችሁ በተሻለ ተግባቦት ልትጓዙ ይገባል ሲሉ የሥልጠና ተሳታፊዎችን በማሳሰብ ሥልጠናውን ለአዘጋጀው ለአክስዮን ማኅበሩ የሰው ሃብት አስተዳደር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሥልጠናው ለሁለት ቀናት ለ45 ሰዎች የተሰጠ ሲሆን አመለካከትን ወይም አስተሳሰብን ወደ ላቀ ከፍታ ለማሸጋገር ያስችል ዘንድ ተጨባጭ ምሳሌዎችን በማንሳት እና መመሪያ በመስጠት የተካሄደ ነው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ወልድያ ላይ ለሚከፈተው የአቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ለተቀጠሩ አዲስ ርዕሰ መምህራን፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች በሥራ ላይ መኖር ስለሚገባ አመለካከት እና ሙያዊ ሥነ ምግባር፣ የአክስዮን ማኅበሩ አደረጃጀት፣ ራዕይ፣ ተልኮ እና የድርጅቱ የስራ ባህል ምን ይመስላል የሚለው ላይ ትኩረት በማድረግ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡