የአቡነ ጎርጎርዮስ ደብረሲና ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ተመረቀ

በ2015ዓ.ም ከተከፈቱ ሁለት ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው የደብረሲና ቅዱስ እግዚአብሔር አብ አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት የአዲስ አበባ እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሆኑት ብጹዕ አቡነ መልከጼዲቅ በታላቅ ድምቀት ተመረቀ፡፡
የምርቃት መርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መልከጼዲቅ፣ መላከ ገነት ቆሞስ አባ ገብረስላሴ ገ/ሚካኤል የደብረ ሲና ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ፣ መላከ ምህረት ቀሲስ በቃሉ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርት መምሪያ ኃላፊ፣ መጋቤ ሰናያት የቻለው ለማ የአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪጅ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አባቶች፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ የሥራ ኃላፊዎች እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት መጋቢ ሃብታት እስጢፋኖስ ሀይሉ የሥራውን አጠቃላይ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ወላጆች ልጆቻቸው በዘመናዊ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊም ታንጸው በሁለት በኩል የተሳሉ እንዲሆኑ መፈለጋቸውን በሂደቱ የተረዳንበት ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም ቀጣዩን ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ በመግለጽ ለቀጣይ ዓመት 40 ክፍሎች ያሉት ህንጻ ለመገንባት እና እስከ 12ኛ ክፍል ለማሳደግ እንደተዘጋጁ የልማት ኮሚቴ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
የኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ(በትምህርት ዘርፍ) የሆኑት አቶ ዘሪሁን ክብረት በመድረኩ ባደረጉት ንግግር አክሲዮን ማኅበሩ ዘርፈ ብዙ ዓላማዎች ያሉት ሲሆን ከሁሉም በላይ በትምህርቱ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት 10 ዓመታትን እንዳስቆጠረ ተናግረዋል፡፡
ጨምረውም የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች አሁን ያለበትን ብቻ ሳይሆን ነገ ሊደረስበት የሚፈለጉ ዕቅዶች እንዳሉት በመጥቀስ ከጀማሪ እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ የራሱ መለያ /ብራንድ/ ያለው ሞዴል ትምህርት ቤት መሆንና ለሀገር እና የቤተ ክርስቲያኗን ዓላማ ማስፈጸም የሚችል ትውልድን የሚተካ ትውልድ በጥራት ለማፍራት እየተጋ ያለ ተቋም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተለያዩ ዝግጅቶች የቀረቡ ሲሆን ወረብ፣ ቅኔ፣ ግጥም እና ዝማሬዎች እንዲሁም መጋቢ አእላፍ ኤፍሬም በየነ የእግዚአብሔር ቃልን አካፍለዋል፡፡
ትምህርት ቤቱ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሰባተኛ ክፍል የሚያስተምር ሲሆን 816 ተማሪዎችን መዝግቦ በማጠናቀቅ ሥራውን ጀምሯል፡፡
ደረጃውን የጠበቀ የመማሪያ ክፍሎች እና ለተማሪዎች ምቹ የሆነ ምድረ ግቢ ያለው የደብረሲና ቅዱስ እግዚአብሔር አብ አቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት በግብዓትም በስፋትም የተደራጀ ቤተ-መፅሀፍት፣ ቤተ-ሙከራ እና የትምህርት ማበልጸጊያ ማዕከል የሚገኝበት ነው፡፡
ዛሬ የተመረቀውን ቅርንጫፍ ከአጠቃላይ አቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች በሁሉም ዘርፍ ተምሳሌት ለማድረግ እየተሰራ ሲገኝ ውጤታማ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ተማሪዎች የሚፈሩበት እና በትምህርት አሰጣጡ በተማሪ፣ በወላጅ እና በመምህራን ተመራጭ ለማድረግ በትጋት ይሰራል፡፡
የግንባታውን ሂደት ለማጠናቀቅ 9,806,514 ብር የፈጀ ሲሆን ግንባታው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽዎ ላደረጉ አካላት የምስጋና ስጦታ ተበርክቷል፡፡ በመጨረሻም በመርሃ ግብሩ የታደሙ እንግዶች የመማሪያ ክፍሎቹን ጎብኝተዋል፡፡