‹‹የአውሮፕላን ዲዛይን የመሥራት የወደፊት ዕቅዴ ነው›› /ታዳጊ ቅዱስ የሺዋስ/

‹‹የአውሮፕላን ዲዛይን የመሥራት የወደፊት ዕቅዴ ነው›› /ታዳጊ ቅዱስ የሺዋስ/

በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ሰምና ወርቅ ባዘጋጀው የአቡነ ጎርጎርዮስ ተማሪ የሆነው ታዳጊ ቅዱስ የሺዋስ ‹‹የአውሮፕላን የበረራ ምስጢሮች›› የተሰኘውን መጽሐፍ ለምርቃት አብቅቷል፡፡
መጽሐፉ አሥራ ሁለት ምዕራፍ ያለው ሲሆን ስለ አውሮፕላን ታሪክ፣ የአውሮፕላን ምንነት፣ አራቱ ኃይሎች፣ የአውሮፕላን አካላት፣ የበረራ መቆጣጠርያ ክፍል፣ የአውሮፕላን ዓይነቶች፣ ከድምጽ ፍጥነት በላይ፣ የአውሮፕላን ምስጢራዊ እውነታዎች፣ የአውሮፕላን ሞተር፣ ሄሊኮፕተር፣ የአውሮፕላን አብራሪ እና አውቶ ፓይለት የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ተዳሰውበታል፡፡ መጽሐፉ 76 ገጽ ሲኖረው በምስል የተደገፉ ማብራርያዎች ታክሎበታል፡፡በመጽሐፉ አስተያየት ከሰጡት መካከል የአውሮፕላን የጥገና ባለሙያ የሆኑት ኤልያስ አብራር ‹‹ከዕድሜው የፈጠነ ግንዛቤና ብስልት የተዘጋጀ ነው፡፡ የአውሮፕላንን ምንነት፣ ጥቅም፣ አሠራሩን እንዲሁም ለመንቀሳቀስ የሚረዱትን ሳይንሳዊ እውነታዎች የሚያስረዳ መረጃ የያዘ መጽሐፍ ነው›› በማለት ምስክርነታቸውን ገልጸዋል፡፡
የታዳጊ ቅዱስ የሺዋስ እናት የሆኑት መምህርት ሙሉ ብርሃን ‹‹ልጄ ቅዱስ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የልጅ አዋቂ፣ በትምህርቱ ጎበዝ፣ አመለ ሸጋ፣ መልከ ቀና፣ ለእውቀት የሚጎጎ ልጅ ነው፡፡ በትምህርቱ የደረጃና ተሸላሚ ተማሪ ነው፡፡ በሕፃን እጁ ራሱ ጽፎ ያዘጋጀው መጽሐፍ ለሌሎች በማበርከቱ እጅግ ደስተኛ ነኝ›› ብለዋል፡፡
ወላጅ አባቱ ፖለቲከኛ የሺዋስ አሰፋ ‹‹የአውሮፕላን የበረራ ምስጢሮች›› በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን መጽሐፍ በ2024 ሁሉም ሰው ሊጠቀምበት የሚችል ኤርካር በራሱ ዲዛይን ለመሥራት ያስቀመጠውን ርዕይ ነው በመጽሐፍ ያዘጋጀልን፡፡ ርዕዩን ለማሳካት ሥራው በሁሉም ኢትዮጵያውያንና ሌሎችም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ወዳጆች እንዲነበብለት እመክራለው›› ሲሉ ስለልጃቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ታዳጊ ቅዱስ የሺዋስ ‹‹እንደ መኪና የምታገለግል አውሮፕላን መሥራት የወደፊት ርዕዩ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን በአሁኑ ወቅት መኪና ብዙ ሰዎችን እየጠቀመ እንደሆነ ሁሉ የእኔንም የአውሮፕላን ዲዛይን ብዙ ሰዎች እንደ መኪና እንዲጠቀሙበት ማድረግ እፈልጋለሁ›› ብሎናል፡፡

ታዳጊ ቅዱስ የሺዋስ

ታዳጊ ቅዱስ የሺዋስ

የአክሲዮን ማህበራችንን ድህረ ገፅ https://esdros.com/e/ እና በፌስቡክ ገፃችን https://www.facebook.com/Esdros-Construction-Trade-and-Industry-SC-282021025628947 በመከታተል ወቅታዊ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡