የክረምት መርሃ ግብር በሁሉም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች ተጀመረ

የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች የክረምት መርሃ ግብር ትምህርት በሁሉም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች መስጠት ጀመረ፡፡
መርሃ ግብሩ በሁለት መልኩ የሚሰጥ ሲሆን ይህም የቀለም ትምህርት ላይ ያተኮረ ልጆች ባላቸው የክፍል ደረጃ መደበኛ ትምህርት የሚማሩት ዘርፍ ሲሆን ሌላው ደግሞ ከቀለም ትምህርት በተለየ መልኩ የአብነት፣ የግእዝ፣ የእንግሊዘኛ እና የሂሳብ ትምህርቶችን አጠቃሎ የሚማሩበት አይነት ነው፡፡
የወይራ አቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ም/ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ወንድሙ ወ/መስቀል በመርሃ ግብሩ ቀጣይ ዓመት ተማሪዎቹ የሚገቡበት ክፍል እንዳይከብዳቸው ታስቦ ለአንደኛ፣ ለስድስተኛ እና ለስምንተኛ ክፍል ቀድሞ ዝግጅት ለማድረግ ትምህርቱ እየተሰጠ አንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዚህም በአዲሱ ፍኖተ ካርታ መሰረት በቀጣይ ዓመት ስድስተኛ እና ስምንተኛ ከፍል ላይ የሚኒስትሪ ፈተና በመኖሩ ተማሪዎቹ ቅድመ ዝግጅታቸውን አስቀድመው የሚጀምሩበት ስለሆነ መደበኛ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ሲገልጹ ሌሎች የክፍል ደረጀዎች ላይ ግን ተማሪዎች በፍላጎት እየተማሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የክረምት ትምህርት ተማሪዎች ለቀጣይ ዓመት ትምህርታቸው መሰረት የሚይዙበት እና ምን አይነት የትምህርት ይዘቶች እንደሚኖሩ ቀድመው የሚረዱበት በመሆኑ መማራቸው ፋይዳውን የጎላ ያደርገዋል፡፡ ታዲያ በዚህ መርሃ ግብር ከሚማሩ ተማሪዎች መካከል የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ራኬብ እንግዳወርቅ አንዷ ስትሆን የክረምት ትምህርቷን መሟሯ እና ቀድማ መጀመሯ የሚኒስትሪ ፈተና ተፈታኝ እንደመሆኗ ትልቅ አስተዋጽዎ እንዳለው በማንሳት ደስተኛ እንደሆነች ገልጻለች፡፡
እንዲሁም ተማሪ ራኬብ ክረምትን እቤት ከማሳለፍ ይልቅ በትምህርት ማሳለፏ እውቀትን እንድትጨብጥ እንደሚያደርጋት በመጥቀስ ለሚፈተኑት ፈተና እየተዘጋጁ እና እየበረቱ እንዲሄዱ ስለሚያደርግም ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብላለች፡፡
እንደ ም/ርዕሰ መምህሩ ገለጻ የክረምት ጊዜያቸውን ተማሪዎች እዚህ ማሳለፋቸው የቀለም ትምህርታቸውን ከማሻሻል ባለፈ የባህሪ ቀረጻ ላይ ትልቅ አስተዋጽዎ እንዳለው የተናገሩ ሲሆን ልጆች ክረምትን እቤት በሚውሉበት ጊዜ ወቅቱ ውጪ ወጥቶ ለመጫወት አመቺ ባለመሆኑ ጊዜያቸውን ቴሌቪዥን እና ሞባይል ላይ በማሳለፍ አይምሮ ጤናቸው ላይ ትልቅ ጉዳት እንደሚያሳድርባቸው በማንሳት ውጪ ወጥተው ተንቀሳቅሰው መግባታቸው ግን አይምሮአቸው ላይም ሆነ አካላዊ ጤናቸው ላይ ትልቅ አስተዋጽዎ እንደሚኖረው አቶ ወንድሙ ገልጸዋል፡፡
ተማሪ ጀርሚያ አዲሱ የ5ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ክረምቱን ከቀለም ትምህርት ውጪ የአብነት፣ የግእዝ እና የቋንቋ ትምህርቶችን እየተማረ እንደሚገኝ በመግለጽ እንዲዚህ አይነት ትምህርቶችን መማሩ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚሰጠው በመጥቀስ ስለ ሐይማኖቴ እንዳውቅ እና ያለኝን ሥነ ምግባር እንዳዳብር ያግዘኛል ብሏል፡፡
በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የክረምት መርሃ ግብር ለግማሽ ቀን ሲሆን እስከ ነሐሴ 27/2014ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል፡፡

Abunegorgorios