በመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የስራ ክንውን ላይ ውይይት ተካሄደ
በአቡነ ጎርጎርዮስ አዋሬ አንደኛ ደረጃ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት አጠቃላይ የስራ ክንውን እና የሁለተኛ መንፈቅ አመት የስራ አቅጣጫ ላይ ከወላጆች ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡
ውይይቱ የመማር ማስተማር ሂደት፣ የተማሪ የትምህርት አቀባበል፣ የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የተማሪዎች ውጤት ላይ አትኩሮ የተካሄደ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ያሉ ጠንካራ ጎኖች እና ክፍተቶች በስፋት ተዳሰዋል፡፡ በዚህም ተከታታይ የፈተና ምዘናዎች ጥራቱን በጠበቀ ሂደት መካሄዳቸው፣ ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ድጋፍ መደረጉ እና ዝቅተኛ ውጤት ባስመዘገቡ ተማሪዎች ላይ ከወላጅ ጋር ምክክር በማድረግ ለውጥ መምጣት መቻሉ ከተጠቀሱት ጠንካራ ጎኖች መሃከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
እንዲሁም ወላጆች ሁሉንም ኃላፊነት ትምህርት ቤቱ እንዲወጣ መፈለጋቸው፣ በአንዳንድ ተማሪዎች እና መምህራን መካከል የተግባቦት ችግር መፈጠር ፣ የትምህርት ቤቱ የወላጅ ተማሪ መምህራን ህብረት(ወተመህ) በአግባቡ አለመደራጀት እንደ ክፍተት ከተነሱት መካከል ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም በመድረኩ በሁሉም የክፍል ደረጃ የውጤት ትንተና በትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በሆኑት በአቶ ደረጄ በቀለ ተሰርቶ የቀረበ ሲሆን ዝቅተኛ ውጤት በታየባቸው የትምህርት አይነቶች እና ክፍተት በታየባቸው የክፍል ደረጃ ላይ ወደፊት ለመስራት እቅድ ተይዟል፡፡
ወላጆች የተማሪ ቁጥር ከምድረ ግቢው ጋር አለመጣጣሙን በመግለጽ የግቢን ጥበት እንደ ችግር ያነሱ ሲሆን እንዲሁም ከትምህርት ቤቱ ውጪ የሚገኙ መንገዶች ምቹ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተነሱት ሃሳቦች ላይ ውይይት በማድረግ መድረኩ የመፍትሄ ሃሳቦችን ያስቀመጠ ሲሆን ከነዚህም መካከል የትምህርት ቤቱን አላማ እና እሴት ላልተረዱ አንዳንድ ወላጆች እና መምህራን ስልጠና መስጠት፣ብልሹ ሰነምግባር ባላቸው አንዳንድ መምህራን እና ተማሪዎች ላይ የእርምት እርምጃ መውሰድ፣ በትምህርት ጥራት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚመለከታቸው አካት ጋር በጋራ መስራት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ በእለቱ ጠንካራ ወ.ተ.መ.ህ በትምህርት ቤቱ አለመኖሩን በመገንዘብ የነበረውን የማደራጀት ስራ የተከናወነ ሲሆን 7 አባላት በኮሚቴነት ተመርጠዋል፡፡ እንዲሁም የታዩ ክፍተቶችን በመገንዘብ እና የትምህርት ሂደቱን ለማሳለጥ የተማሪዎች፣ የወላጆች፣ የመምህራን እና የባለድርሻ አከላት በጥምረት መስራት ውጤታማ እንደሚያደርግ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡