ስለ ኤስድሮስ

በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ የኖሩት ሀገር በቀል ዕውቀት ባህል በሁሉም ኅብረተሰብ ዘንድ እንዲዳብር ሰፊ ሥራ ለሠሩት አባት አባ ኤስድሮስ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በስማቸው የተሰየመው ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ በተለያዩ ዘርፎች በመሰማራት ሥራዎችን ለመሥራት ታስቦ በ2004 ዓ.ም. በ12 ባለአክሲዮኖች ተቋቋመ።

ርዕይ

ዕሴትን በሚፈጥሩ፣ ትምህርት ላይ በማተኮርና ዘርፈ ብዙ የንግድ ሥራዎች ላይ በመሠማራት በ2030 የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት አሳክቶ ማየት፡፡

ተልእኮ

በምግባር የታነጹ በዕውቀት የበለጸጉ ተማሪዎችን ማፍራት እና ዕሴት የሚጨምሩ ምርት እና አገልግሎት ማቅረብ፡፡

ዕሴቶች

 • አርቆ አሳቢ አመራር
 • ሁሉአቀፍ ውጤታማነት
 • መማር ላይ ያተኮረ ልሕቀት
 • ልዩነትን ማክበር
 • ተጠያቂነት
 • ሌሎች፡- ግልጸኝነት፣ ታማኝነት፣ ሀቀኝነት፣ መተባበር፣ ሁሉን አቀፍ ከባቢያዊ ትኩረት

የተቋሙ አደረጃጀት እና ዓላማ

ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ በሀገራችን የንግድ ሕግ መሠረት ተደራጅቶ በሥሩ በ2007 ዓ.ም. የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ሥራ ጀምሯል። እንደ ማንኛውም አክሲዮን ማኅበር  ኤስድሮስ የሚመራው በዲሬክተሮች ቦርድ ነው። የተሠማራበትን ዓላማ በአግባቡ እንዲፈጽም ለማስቻል በተለያዩ ጊዜያት ካፒታሉን ያሳደገ ሲሆን አክሲዮን ማኅበሩ ሲመሠረት የነበረው 100,000 ብር ካፒታል በአሁኑ ወቅት ብር 174,997,000 የተከፈለ ካፒታል አለው። አጠቃላይ 3035 ኢትዮጵያዊ የሆኑ ባለአክሲዮኖች አደራጅተውታል።

አክሲዮን ማኅበሩ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ እና ባሕርዳር ከተሞች 22 ቅርንጫፍ ት/ቤቶችን በመክፈት 14,823 ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛል። በትምህርት ሴክተር ብቻ ለ1200 ቋሚ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሮ እያስተዳደረ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ከሚገኙት አምስት ቅርንጫፎች ውስጥ ሦስቱ ድርጅቱ ራሱ የገነባቸው ሕንፃዎች ሲሆኑ ሌሎቹ በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ እና ባሕርዳር ከተሞች የሚገኙ ቅርንጫፎች በጊዜያዊነት ተከራይተን የምናስተምርባቸው
ናቸው።

አክሲዮን ማኅበሩ የተመሠረተው እንደማንኛውም የቢዝነስ ድርጅት ትርፍ በማትረፍ ለባለአክሲዮኖች  ለማከፋፈል ሳይሆን ትውልድን የሚተካ ትውልድ ለማፍራት ነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በየዓመቱ ድርጅቱ ለትምህርት አገልግሎት የሚያወጣውን ወጪ መመልከት ይቻላል። በአማካይ የተሰብሳቢውን 96 በመቶ  ለትምህርት አገልግሎት ወጪ በማድረግ ስኬታማ የሆኑ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል።

የተቋሙ ዓላማዎችም፡-

 1. ኢትዮጵያዊ እሴት፣ ባህል እና ስነ ምግባር ለትውልድ ሁሉ ማስተዋወቅና ማስጠበቅ
 2. በኢትዮጵያዊ ማንነቱ የሚኮራ ሌሎችን መሆን የማይሻ ትውልድ ማፍራት
 3. በእውቀትና በክህሎት /ሀገራዊና አለማቀፋዊ ቋንቋዎች፣ የማሰብ፣ የመምራት/ ብቃት ያለው ተወዳዳሪ የሆነ ትውልድ ማፍራት
 4. በስነ ምግባሩ ለትውልድ ሁሉ አርአያነት ያለው ትውልድ በመፍጠር ሂደት ውስጥ የድርሻውን መወጣት ናቸው፡፡

 

ኤስድሮስ የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት

ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር ከተመሠረተባቸው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል ቅድሚያ የሚሠጠው በሀገራችን የትምህርት ሴክተር ተሠማርቶ አንድ የትምህርት ተቋም ሊያከናውናቸው የሚገባ ሥራዎችን መሥራት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኤስድሮስ በሁሉም ተግባራት ከፍተኛ የሆነ ለውጥ በማምጣት ላይ ይገኛል፡፡ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

 1. ብዙ ምሁራን እንደሚሰማሙበት የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ችግር ከነባሩ የትመህርት ሥርዓት ጋር የተጣጣመ ባለመሆኑ ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት የሚያስፈልጋት ትውልድ መፍጠር አልተቻለም፡፡ ስለሆነም ይህን ክፍተት ለመሙላት ከሚጥሩ ተቋማት መካከል አንዱ በመሆን የድርሻችንን በመወጣት እንደሀገር የሚያስፈልገንን ትውልድ ለመፍጠር ከፍተኛ ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ለተማሪዎች ሥልጠናዎች ይሠጣሉ፡፡ ነባሩ ትምህርት የሚሰጥበትን ስልት (Teaching Methedology) በማጥናት ዘመናዊ ትምህርቶችን ለማስተማር እንጠቀምበታለን፡፡ በረጅሙ የስነ ጽሑፍ ታሪካችን ሀገራችን በአግባቡ ሰንዳ ያስቀመጠቻቸውን ሰነዶች እና መጻህፍትን ተማሪዎች እንዲመረምሩ ታሪካቸውን እና ማንነታቸውን እንዲያውቁ ይደረጋል፡፡ በዚህም በማንነታቸው የሚኮሩ፣ በእውቀት የበለጸጉ እና ሀገራቸውን የሚወዱ ተማሪዎችን አፍርተናል፡፡
 2. በተለያዩ ጥናቶች እንደተረጋገጠው በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች ገና በለጋ ዕድሜያቸው ለተለያዩ ሱሶች እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡ አብዘሀኛው ዜጋችን ወጣት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሩ ለሀገራችን ከባድ ፈተና ነው፡፡ በወጣቶች ሕይወት እየተለመደ የመጣው ይህ ችግር በመንግስት እና አርቀው በሚያስቡ ተቋማት መፈታት ካልተቻለ ሀገርን ማሳደግ አይቻልም፡፡ በተግባርም ከፍተኛ የሆነ ጥፋት እያስከተለም ይገኛል፡፡ በእርግጥ በወጣቶቻችን ላይ የገጠመን ችግር መነሻው የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩትም የትምህርት ተቋማት ትኩረት ማነስ፣ ተገቢውን ክትትል አለማድረግ፣ ለተማሪዎች ተጨማሪ ሥልጣናዎችን አለመስጠት እንደ ዋና ምክንያትነት ይነሳሉ፡፡ አስድሮስ የዜጎችን የስነምግባር እና ግብረገብን ግንዛቤ ሊያዳብሩ የሚችሉ መጻሕፍትን በማዘጋጀት እና በማስተማር የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡
 3. በተለይ የግል ትምህርት ቤቶች ለውጭ ሀገራት ቋንቋ ብቻ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ማስተማራቸው ተማሪዎች አካዳሚያዊ እውቀታቸው ከመዳከሙ ባሻገር በሀገራቸውና በማንነታቸው እንዳይኮሩ፣ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንዳይኖራቸው፣ ለሀራቸውና ለሕዝባቸው ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ እየሆን እየተደረገ ስለሆነ እና ይህም ክፍተት አሳሳቢ ስለሆነ ችግሩን ከመፍታት አኳያ የድርሻችን ለመወጣት፣
 4. አብዛኛዎቹ የትምህርት ተቋማት እና ወላጆች አካዳሚየሳዊ ትምህርት ላይ ብቻ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ ሌሎች ተጓዳኝና አስፈላጊ ጉዳዮችን ትኩረት አለመስጠታቸው ለምሳሌ ለግብረ ገብ ትምህርት ያላቸው ትኩረት በጣም ዝቅተኛ መሆን ተማሪዎች በሥነ- ምግባር ያልጎለበቱ ሆነው እንዲያድጉ አድርጓቸዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ለግብረ ገብ ትምህረት ትኩረት አልታሠጠም፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች ለኢትዮጵያዊ እሴቶች እንግዳ ናቸው፡፡ ጨዋነት፣ ቸርነት፣ ተባበሪነት፣ ሰውን አክባሪነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ በመተሳሰብ እና በመከባበር አብሮ መኖር፣ የወገን እና የሀገር ክብር ማስቀድምና ማክበር እና የመሳሰሉት በትውልዱ ላይ እየታዩ አይደለም፡፡ ይህን ክፍተት ለማስተካከል አርቆ አስቦ እና ተደራጅቶ መሥራትን ስለሚጠይቅ ኤስድሮስ በመመሥረት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በተለይ ሌሎች የትምህርት ተቋማት የእኛን ተሞክሮ እንዲከተሉ ለማድረግ ስልጠናዎችን በመስጠት እና የማስተማሪያ ግብዓቶችን በድጋፍ በመስጠት ከፍተኛ ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡