ዋና ዋና ተግባራት
አክሲዮን ማኅበሩ ወጣቱን ትውልድ ሀገር ወዳድና መልካም ዜጋ አድርጎ በማነፅ ላይ በትኩረት ይሠሩ ለነበሩት ኢትዮጵያዊ አባት አቡነ ጎርጎርዮስ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ በስማቸው በሰየማቸው ትምህርት ቤቶች ሥራውን በ2007 ዓ.ም. የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የ22 ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች ባለቤት መሆንም ችሏል።
በባሕርዳር፣ ድሬዳዋ እንዲሁም በአዲስ አበባ በሚገኙት ት/ቤቶቹ ኤስድሮስ ኮ.ን.ኢ አ.ማ 14,823 ተማሪዎችን ዕውቀት እየመገበና በሥነ ምግባር እያነፀ ትውልድን የሚተካ ትውልድ በተሻለ ጥራት የማፍራት ሀገራዊ ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።
ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ በሪልኢስቴት ልማት ዘርፍ በመሰማራት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤቶች እጥረት ለመቅረፍ በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ‘‘ሃያ ሁለት’’ እየተባለ በሚጠራው ቦታ አካባቢ በ2011 ዓ.ም. የግንባታ ቦታ በመግዛት ሦስት ቤዝመንቶች፣ አንድ ግራውንድ እና 15 ወለሎች ያለው ዘመናዊ ሕንፃ በመገንባት ላይ ይገኛል።
አክሲዮን ማኅበሩ የሪልኢስቴት ዘርፉን አጠናክሮና ራሱን አስችሎ ለማስኬድ ያመቸው ዘንድ ስትራቴጂክ ፕላን በማውጣት በርካታ ሥራዎችን እየሠራም ይገኛል። በቀጣይም በርካታ አካባቢዎችን ለማልማት በዕቅድ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
አክሲዮን ማኅበሩ በሰበታ ቦታ ላይ ሊሰማራበት በእንቅስቃሴ ላይ ለሚገኘው የሌብሊንግ ዘርፍ ማሽነሪዎች ግዢ ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት አቅራቢውን ድርጅት የመረጠ ሲሆን ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በፈቀደው ብድር ለማደስ የአዋጭነት ጥናት በመከለስ ለባንኩ አቀርቦ ምላሽ በመጠበቅ ላይ ይገኛል ።