ተማሪ ስምኦን ደረጄ የ11ኛ ክፍል ተማሪ በርካታ የፈጠራ ስራዎችን መስራት የቻለ ታዳጊ ሲሆን የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች አዋሬ ቅርንጫፍ የተማሪዎቹን የፈጠራ ስራዎች ለወላጅ ፣ ለመምህራን እና ለተማሪዎች ባሳየበት መድረክ ላይ ስራዎቹን ለዕይታ ካቀረቡት ተማሪዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ በዕለቱ ልክ እንደ ስምኦን በተለያዩ ተማሪዎች የተፈጠሩ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰሩ ድረ ገጾችን፣ ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ውጤቶችን እና ተሰጥኦ ባላቸው ተማሪዎች የተሳሉ ስእሎችን ለእይታ አቅርቧል፡፡
ወ/ሮ የምስራች ዘውዱ የትምህርት ማበልጸጊያ ማዕከል ኃላፊ ሲሆኑ ተማሪዎቹን በሚፈልጉት ዘርፍ እና ባላቸው ተሰጥኦ አስቀድመው በመለየት ወደ ስራ እንደሚገቡ የገለጹ ሲሆን ተማሪዎቹ በሚያስፈልጋቸው ሁኔታ የግብአት ድጋፍ በማድረግ እንደሚያግዟቸው ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎቹ የቁርስ እና የምሳ ሰአታቸውን እንዲሁም ባላቸው የትርፍ ሰአት የፈጠራ ስራዎችን እንደሚሰሩ እና በዚህም ውጤታማ የሆኑ ፈጠራዎችን በመስራ ላይ እንደሚገኙ እና በሚወዳደሩባቸው መድረኮችም በስራዎቻቸው አሸናፊዎች ናቸው ብለዋል፡፡
የተማሪ ወላጅ አባት የሆኑት አቶ በትግሉ በቃሉ በዕለቱ የፈጠራ ስራዎቹን የጎበኙ ሲሆን በጽንሰ ሃሳብ የተማሯቸውን እንደዚህ በተግባር ሰርተው ማየታቸው እንዳስደነቃቸው እና ያላቸው ፍላጎት የቱ ጋር እንደሆነ በደንብ የተለየበት ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም በተማሪዎቹ የተሰሩት ድረ ገጾች በደንብ የተዳራጁ እንደነበሩ እና እነዚህ ፈጠራዎች በበጀት እጥረት ምክንያት ወደ መሬት ወርደው ላናያቸው እንችላለን የሚል ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ቀርበው የነበሩት የፈጠራ ስራዎች በተማሪዎቹ ገለጻ ሲሰጥባቸው የነበረ ሲሆን እንደዚህ የፈጠራ ስራዎችን መስራታቸው የአይምሮ መነቃቃትን ይፈጥርላቸዋል ብሎም ነገ ደግሞ ወደ መሬት አውርደው ጥቅም ላይ ያውሉታል ሲሉ ወ/ሮ የምስራች የገለጹ ሲሆን እንዲሁም ያላቸውን የፈጠራ ስራዎች የሚያዳብሩበት ነው ብለዋል፡፡ ጨምረውም የግብአት እጥረት እንዳለ ገልጸው አቅርቦት ቢኖር ተማሪዎቹ ከዚህ የበለጠ የመስራት አቅም እንዳላቸው እና ለትምህርት ቤቱም ሆነ ለሀገር የሚጠቅም ፈጠራን ማበርከት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
በውሃ ሃይል የሚሰራ ፍሪጅ፣ በኤሌክትሪክ እና በባትሪ መስራት የሚችል ወንፊት ፣ የትምህርት ቤታቸውን ንጽህና መጠበቅ የሚያስችል ዳስተር ማራገፊያ እና የልጆች መጫወቻ የፈጠራ ስራዎችን በዕለቱ ያቀረበው ተማሪ ስምኦን የፈጠራቸው ስራዎች ከተመለከታቸው ችግሮች በመነሳት እነርሱን ለመቅረፍ አስቦ እንደሆነ የተናገረ ሲሆን ሌሎች ተማሪዎችም በትርፍ ጊዜያቸው የተለያዩ ነገሮችን እንዲሞክሩ እና እውቀታቸውን እንዲያዳብሩ ሲል መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
የአክሲዮን ማህበራችንን ድህረ ገፅ https://esdros.com/e/ እንዲሁም ቴሌግራም https://t.me/Esdrossc በመከታተል ወቅታዊ መረጃዎችን ያገኛሉ።
