የአቡነጎርጎርዮስ ት/ቤቶች በጥያቄና መልስ የውድድር መድረኮች ላይ ብልጫ ማስመዝገባቸውን ቀጥለዋል፡፡
የአቧሬ ቅርንጫፍ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት በአራዳ ክ/ከተማ ወረዳ 7 ከሚገኙ ት/ቤቶች ጋር በተካሔደ የ 8ኛ እና 4ኛ ክፍል የጥያቄና መልስ ውድድር አሸናፊ ሆነ፡፡
የጥያቄና መልስ ውድድሩ የቀለም ትምህርቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን በ8ኛ ክፍል ውድድር ላይ 2 ተወዳዳሪዎች ተሳትፈው 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ በተመሳሳይ በ4ኛ ክፍል ውድድር ላይ 2 ተማሪዎች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን እነርሱም 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን ይዘው አሸናፊ በመሆን አጠናቀዋል፡፡
የአቧሬ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ም/ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ወልደማርያም ዘገየ ተማሪዎቹ በውድድር መድረኩ ብልጫን ያሳዩበትና ከሌሎች ትምህርት ቤቶች ጋር ተወዳድረው ያላቸውን አቅም ያዩበት ነበር ብለዋል፡፡
ም/ርዕሰ መምህሩ ጨምረውም ተማሪዎቹ ወደ ውድድር መድረኩ ከመሔዳቸው በፊት ተረጋግተው መመለስና መደናገጥ እንደሌለባቸው ገለፃ ተደርጎላቸው የነበረ ሲሆን በውድድር መድረኩም ተማሪዎቹ ትልቅ ልምድ ያገኙበትና በብልጫ ያጠናቀቁበት ነው ብለዋል፡፡
ሌላው በውድድሩ ማሸነፋቸው ትምህርት ቤት ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሮላቸዋል፡፡ እንዲሁም በቀጣይ ለሚኖሩ ውድድሮች እንዲዘጋጁ አነቃቅቷቸዋል ሲሉ አቶ ወልደማርያም ዘገየ ተናግረዋል፡፡
በያዝነው ወር የአቡነ ጎርጎርዮስ የለቡ እና የወይራ ቅርንጫፍ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች በጥያቄና መልስ ውድድሮች ላይ ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው፡፡
