በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች በባሕርዳር ቀበሌ 11 ቅርንጫፍ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎችን የፈጠራ ሥራዎች የሚያሳይ ዐውደ ርእይ ተዘጋጀ፡፡
በዐውደ ርእዩ ላይ በተማሪዎች የተዘጋጁ የፈጠራ ውጤቶች፣ የባዮሎጅ፣ የኬሚስትሪ፣ የፊዚክስ የላብራቶሪ ውጤቶች ፣በሥነ ጥበብ በተማሪዎች የተሠሩ የፋሽን ዲዛይን፣ ሥዕሎች እና የሕንፃ ዲዛይኖች የቀረቡ ሲሆን በቋንቋ እና ኪነ ጥበብ ዘርፍም በተማሪዎች የተደረሰ “ውርስና መዘዙ” የተሰኘ ቲያትር ለተማሪዎች፣ለመምህራን እና አጠቃላይ ለትምህርት ቤቱ ማኅበርሰብ ለእይታ ቀርቧል፡፡
በፈጠራ ሥራዎች ዘርፍም በተማሪዎች የተሠራ ለአካል ጉዳተኞች በር መክፈት እና መዝጋት የሚያስችል ፈጠራ ለእይታ ከቀረቡ ሥራዎች ውስጥ ይገኛል፡፡
በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች በባሕርዳር ቀበሌ 11 ቅርንጫፍ በተዘጋጀው በዚህ የፈጠራ ሥራዎች ዐውደ ርእይ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ያቀረቡበት ሲሆን በቀጣይም የፈጠራ ሥራዎቹን በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ለማቅረብ ዝግጅት መኖሩን ከባሕርዳር ቀበሌ 11 ቅርንጫፍ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
