የኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ የዋና መስሪያ ቤት ሰራተኞች ከአዲስ አበባ በ60 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደሚገኘው አደሬ ደብረ ሰዋሰው ቅድስት ኪዳነምሕረት ገዳም መንፈሳዊ ጉዞ አካሄዱ፡፡
ገዳሙ በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ በአለልቱ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን የቅድስት ኪዳነምሕረት፣ የሔዋን እና አዳም ጽላትን ጨምሮ አስራ ሰባት የቅዱሳን ጽላቶች በቦታው ከሚገኝ ዋሻ የወጡበት ነው፡፡ ይህም ከገዳም አባቶች መረዳት እንደተቻለው በጥንት በግራኝ መሐመድ ዘመን አባቶች ዋሻ ውስጥ ደብቀውት የሄዱት ጽላት እንደሆነ ታውቋል፡፡
የአደሬ ደብረ ሰዋሰው ቅድስት ኪዳነምሕረት ገዳም ስያሜውን ያገኘው ጻድቁ አቡነ ተክለሐይማኖት ስፍራው በትውልድ አካባቢያቸው የሚገኝ በመሆኑ አድረው ጸሎት በማድረጋቸው አደሬ የሚለውን ስያሜ ሊይዝ ችሏል፡፡ በመሆኑም አባቶች በራዕይ በማየት በገዳሙ በ1974ዓ.ም ቅድስት ኪዳነምሕረት ከዋሻ ወጣች በ1983 ዓ.ም ደግሞ ወደ አነስተኛ መቃኞ ውስጥ ገባች፡፡ ከዚያም በ 1985 ዓ.ም በአቡነ ኤፍሬም ቡራኬ ተገደመች በመጨረሻም በጥር 16/2002ዓ.ም በአቡነ ቀውስጦስ ቡራኬ ወደ አዲሱ ቤተ-መቅደስ እንደገባች በገዳሙ ተጽፎ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ታዲያ በዚህ የተቀደሰ ሥፍራ የዋናው መስሪያ ቤት ሰራተኞች መንፈሳዊ ጉዞ በማድረግ ቦታው ላይ ከፈለቀው ፈዋሽ ጸበል በመጸበል እና በረከትን በማግኘት ታሪካዊውን ገዳም መጎብኘት ችለዋል፡፡
ሰራተኞቹ በገዳሙ በነበራቸው ቆይታ የቤተክርስቲያንን ፈተና ከዘመኑ ጋር እንዴት እንለፈው እና መስዋእት መሆን ምን ማለት ነው በሚሉት ርዕሰ ሃሳቦች ላይ ሰፊ ውይይቶች በማድረግ በመጨረሻም ክርስቲያኑ በጸሎት መትጋት እና በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚንሸራሸሩ ሀሳቦች መወሰድ እንደሌለበት ተጠቁሟል፡፡ እንዲሁም በገዳሙ ቆይታ መንፈሳዊ የጥያቄ እና መልስ ውድድር በሰራተኞች መካከል የተካሄደ ሲሆን ይህም ግንዛቤን ያስጨበጠ ቆይታን ማድረግ አስችሏል፡፡
ስፍራው እጅግ ጸጥታ የሰፈነበት እና በርካታ የቅዱሳን ጽላት የሚገኝበት ሲሆን የዋና መስሪያ ቤት ሰራተኞችም በዚህ መንፈሳዊ ጉዞ ተሳታፊ በመሆን ያላቸውን መንፈሳዊ ጽናት በማዳበር እና የቦታውን በረከት በማግኘት ብሎም የእርስ በእርስ ትስስርን በማዳበር መልካም የሚባል ቆይታን አድርገዋል፡፡
