በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ለሁለት ቀናት የሚቆየው ታላቅ የትምህርት አውደ ርዕይ ዛሬ መጋቢት 17/2014ዓ.ም በወይራ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት በታላቅ ድምቀት ተከፈተ፡፡
የመክፈቻው መርሃግብር የአክስዮን ማህበሩ የቦርድ አባላት፣ የዋና መስሪያ ቤት የስራ ኃላፊዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ የድርጅቱ ሰራተኞች እና የአውደ ርዕዩ አቅራቢ የሆኑ ትምህርት ቤቶች በተገኙበት ተጀምሯል፡፡
የኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ ም/ዋና ስራ አስኪያጅ (በትምህርት ዘርፍ) የሆኑት አቶ ዘሪሁን ክብረት በመክፈቻ ንግግራቸው አውደ ርዕዩ በዋናነት ተማሪዎቹ የሚሞክሩት ሙከራ እና ስራቸው የጋን ውስጥ መብራት እንዳይሆንባቸው ወጥቶ መታየት እንዲገባው ከአምና ጀምሮ ለማሰየት እንደተሞከረ ገልጸዋል፡፡ ዛሬም ሰፋ ያለ ጊዜ እስከ ነገ የሚቆይ መርሃ ግብር ተይዞ የተማሪዎቻችንን ስራዎች ለማሳየት በወላጆቻቸው እና በአጠቃላይ በባለድርሻ አካላት ስራቸው እንዲታይ እደጉ ተብለው እንዲመረቁ እና የትምህርት ቤታችንንም ደረጃ ማየት እንዲቻል በማሰብ እና ለወደፊት አቅጣጫዎቻችን ግብረመልስ መሰብሰብ እንዲያስችል ይህ አውድ ርዕይ እንደተዘጋጀ ተናግረዋል፡፡
በአውደ ርዕዩ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዙሪያ ያሉ ስራዎች፣ የስነ-ጽሁፍ እና ስነ-ጥበብ የተሰጥኦ ውጤቶች የሚቀርቡ ሲሆን እንዲሁም ለእይታ መቅረብ በቻ ሳይሆን ከትምህርት ቤቱ ባለድርሻ አካላት ውጪ በሆኑ ባለሙያዎች ስራቸው እየታየ የውድድር እሳቤን ይዞ በዳኞች በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ ስለዚህም ሁሉም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች እንደየደረጃቸው በአውደ ርዕዩ ይመዘናሉ ሲሉ አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡
በአውደ ርዕዩ የተማሪዎች የፈጠራ ስራ፣ ግጥም ፣ ሥነ ጽሁፍ፣ ቅኔ እና የተለያዩ አስደናቂ ሥራዎች ለዕይታ በመቅረብ ላይ ሲገኙ ተጋባዥ እንግዶችም የተማሪዎቹን ድንቅ ስራዎች በመታደም ላይ ናቸው፡፡
ዛሬ በድምቀት የተጀመረው ይህ የትምህርት አውደ ርዕይ የመዝጊያ እና የሽልማት መርሃግብር በማድረግ በነገው እለት ፍጻሜውን ያገኛል፡፡
በመሆኑም የተማሪ ወላጆች፣ ባለድርሻ አካላት እና መላው የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ አውደ ርዕዩን በመጎብኘት የተማሪዎቹን ስራ በማየት እንዲያበረታቱ እንዲሁም ትምህርት ቤቶቻችን የደረሱበትን ደረጃ ለመገንዘብ እንዲችሉ እስከ ነገ በሚቆየው መርሃግብር ላይ በክብር ተጋብዘዋል፡፡

