በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች የተዘጋጀው የትምህርት አውደ ርዕይ የቦርድ ሰበሳቢ እና አባላት፣ የዋናው መስሪያ ቤት የስራ ኃላፊዎች፣ ወላጆች እና ተጋበዥ እንግዶች በተገኙበት በዛሬው ዕለት በደማቅ የመዝጊያ መርሃግብር ተጠናቀቀ፡፡
በመዝጊያው መርሃግብር በዳኞች የተመረጡ የተማሪዎች የፈጠራ ስራዎች፣ ሥነ-ጥበብ እና ሥነ-ፅሁፍ እንዲሁም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶች ከየቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶቹ በመድረኩ ላይ ቀርበዋል፡፡
የኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ታደሰ አሰፋ በመዝጊያ ንግግራቸው ተማሪዎቻችን መምህራኖቻቸው በየትኛውም አግባብ የሚሰጧቸው ትምህርት በሁሉም መስክ ስለሆነ ይህንን ጠብቀው እውቀት ለመገብየት የሚያደርጉት ጥረት የነገን ተስፋ ያለመልማል ብለዋል፡፡ ጨምረውም ከምንም በላይ ወላጆችን ማመስገን እንደሚፈልጉ ገልጸው እኛን አምናቹ ልጆቻችሁን ስለላካችሁ እኛ ደግሞ ልጆቻችሁን ተቀብለን ወደ ተሸለ ደረጃ የማድረስ ኃላፊነት አለብን ሲሉ እንዲሁም ከወላጅ የሚጠበቀው የልጆቹን አጠቃላይ የትምህርትም ሆነ የስነምግባር ሁኔታ ዕለት ተዕለት መከታተል ነው ብለዋል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ በንግግራቸው ወላጆችን በሚያደርጉት ተግባር ያመሰገኑ ሲሆን በጋራ ከሰራን ልጆቻችን ነገ ሃገር እና ቅድስት ቤተክርስቲያንን ሊረከቡ የሚችሉ ትውልድን እናፈራለን ሲሉ ለአውደ ርዕዩ መሳካት የዋና መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ከቅርንጫፍ ኃላፊዎች ጋር እጅ እና ጓንት ሆነው ሰርተው ይህንን የሚያስደስት ነገር በማቅረባቸው ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም በሁለቱ ቀናት አውደ ርዕይ ቆይታ የተሻለ የፈጠራ ስራዎች፣ ስነ ጥበብ እና ስነ ጽሁፍ ያቀረቡ ተማሪዎች እና በኢንፎርሜሽን ዘርፍ የተሻለ ስራ ላቀረቡ ተማሪዎች እንዲሁም በያዝነው ሳምንት በተደረገው የጥያቄ እና መልስ ውድድር ላሸነፉ ተማሪዎች እና ለአውደ ርዕዩ መሳካት አስተዋጽዎ ላደረጉ አካላት ሽልማት በማበርከት ተጠናቋል፡፡
በዓመት አንዴ በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች በሚዘጋጀው የትምህርት አውደ ርዕይ በዘንድሮው ወይራ ቅርንጫፍ ባዘጋጀው መድረክ የዚህ አመት ትምህርት ቤት አሸናፊዎች በቅድመ መደበኛ ሲኤምሲ ቅርንጫፍ፣ በአንደኛ ደረጃ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ሲያሸንፍ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለቡ ቅርንጫፍ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ዳኝነቱም ፍጹም ፈትሃዊ የነበረና የተማሪዎችን ስራዎች በአግባቡ በማየት የልፋታቸውን ውጤት የመሰከረ ነው፡፡
