በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ተዘጋጅቶ የነበረው የትምህርት አውደ ርዕይ በሁሉም ዘርፍ ስኬታማ ሆኖ እንደተጠናቀቀ ተገለጸ፡፡
የአውደ ርዕዩን በስኬት መጠናቀቅ የኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ ም/ዋና ስራ አስኪያጅ (በትምህርት ዘርፍ) አቶ ዘሪሁን ክብረት የገለጹ ሲሆን ስኬታማነቱ የተቀመጠለትን አላማ ያሳካ መሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ትልቁ ነገር የተማሪዎቹን ተሰጥኦ በሁሉም ረገድ ይዞ መውጣቱ ነው ያሉ ሲሆን ሁሉም አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙት ቅርንጫፎች ቀላል የማይባል ዝግጅት አድርገው ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ስራ ሰርተው ሙያዊ የሚመስሉ ውጤቶችን ያቀረቡበት እና ከአላማው አንጻር ተማሪዎቹ ያላቸውን ተሰጥኦ ይዘው መውጣት የቻሉበት በመሆኑ ውጤታማ የምንለው ነው ብለዋል፡፡
ሌላው አውደ ርዕዩ ከተሳታፊ እና ተጋባዥ እንግዶች አንጻር ሲታይ የትምህርት ቤቱ ባለድርሻ አካላት ከውስጥም ከውጪም ተሳታፊ የነበሩበት፤ በሁለቱ ቀናት ጉብኝት በርካታ ሰው መታደም የቻለበት እና አብዛኛው ሰውም በተመለከተው ነገር ደስተኛ በመሆኑ ለተማሪዎቹ የሰጠው ግብረ መልስ በጣም ጠቃሚ እና ሁሉን ያሳተፈ ነው፡፡
ከውጪ ባለድርሻ አካላት የትምህርት ቢሮ ባለሙያዎች ፣ ከቦርድም መገኘት ያለባቸው አባላት የተገኙ ሲሆን በወላጅም በኩል በርካታ ሰዎች መታደም የቻሉበት እና የራሳቸውን አስተዋጽዎ ያደረጉበት መድረክ ነው፡፡ በመሆኑም በመድረኩ ግድ ማወዳደር ስለነበረ እንጂ ለመለየት የሚከብዱ ስራዎች እንደቀረቡ የታየበት ስለመሆኑ አቶ ዘሪሁን ሲገልጹ ትልቁ ነገር ማንነታቸውን እና አቅማቸውን ለማሳየት ማወዳደር ቢኖርብንም የእነሱ ውጤት ግን ከጣት ጣት የማበላለጥ ያህል እንደነበረ በማንሳት ልፋታቸው ስኬታማ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ሰዎች በደከሙት ድካም ልክ እውቅና መስጠት ተገቢ በመሆኑ ሁሉም እንደየስራው ተቀባይነትን ያገኘበት መድረክ ነው፡፡ ሽልማቱን አንዱ ቅርንጫፍ በቡድን ሲሸለም ሌላው በግል ሲወስድ የታየ ሲሆን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በያንስ በአንድ ዘርፍ ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ትምህርት ቤቶቹ ያሉበትን ደረጃ ለመለየት አስቸጋሪ መሆኑ የሚገኙበት ደረጃ የተቀራረበ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ በሁሉም ቅርንጫፎች የሚሰራው ስራ ተመሳሳይነት እንዳለው መገንዘብ የተቻለበት ሁኔታ ሲፈጠር በሁሉም ዘርፍ እውቅናን ለመስጠት በተካሄደው ሂደት ውጤታማ ስራ መሰራቱን ም/ዋና ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
የአውደ ርዕዩ ሌላው ትልቁ መልካም ገፅታ አንዱ ቅርንጫፍ ከሌላው ልምድ የተለዋወጠበትን መድረክ መፍጠሩ ሲሆን ሁሌም በየወሩ ልምድ ልውውጥ የሚደረግ ቢሆንም ይህኛው የተማሪዎች ልዩ ተሰጥኦዎችን የሚመለከት ስለሆነ ብዙዎቹ ተግባራት መነሳሳትን የፈጠሩበት እና በሽልማቱ ሂደትም አንዱ ሲሸለም ሌላው ሲቆጭ የተመለከትንበት ነው፡፡ ይህም መሆኑ ለቀጣዩ ዓመት ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር ሲሆን ከዓመት ዓመት መሻሻሎችን የምናይበት ልምድ ያተረፍንበት እና የተሻለ ስራ የተሰራበት መሆኑ ውጤታማ ደረጃን የምንሰጥበት ነው ሲሉ አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡
የአውደ ርዕዩ ቀን ማጠሩ የተማሪዎቹን እጅግ አስደናቂ የሆኑ በርካታ ስራዎችን በጥልቀት ለመጎብኘት ባለመቻሉ ሰፋ ያለ ጊዜ መያዝ እንዳለበት ትምህርት የተወሰደበት እንዲሁም ከፈጠራ ስራዎች አንጻር በቀላሉ እገዛ ቢደረግላቸው የበለጠ ጥራት ማምጣት የሚችሉ ስራዎች እንደነበሩ ግንዛቤ የተወሰደበት እና በቀጣይ እገዛ ማድረግ እንደሚገባ ስራዎችም የበለጠ መጠንከር እንዳለባቸው የተወሰደበት መድረክ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአጠቃላይ ድጋፍ ከሚያደርጉ አካላት ጋር እነዚህን የፈጠራ ስራዎች አእምሮአዊ ሃብት አድርጎ ለማስቀረት እና አስመዝግቦ የመሄድ ስራን መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ተማሪዎቹ በመድረኩ እንደተመለከትናቸው ትልልቅ ስራዎችን ያቀረቡ ሲሆን ድርጅቱ የሳይንስ ማዕከላትን አቋቁሞ ትኩረት በመስጠት እነዚህን ሳይንሳዊ የሆኑ ስራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በማገናኘት ለማሳደግ እንደሚጥር በመግለፅ ም/ዋና ስራ አስኪያጅ (በትምህርት ዘርፍ) የሆኑት አቶ ዘሪሁን ክብረት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡
የዚህ ዓመት አውደ ርዕይ ውጤታማ በሚባል ደረጃ በድምቀት የተጠናቀቀ ሲሆን ለቀጣይ ዓመት ዝግጅት ጥሩ ልምድ የተወሰደበት እና እጅግ መልካም የሚባሉ የልምድ ልውውጦች እና ተሞክሮዎች በቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች መካካል የተካሄደበት ነው፡፡
