ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ.

ስርቆትን የሚጠየፍ ትውልድ እናፍራ

ስርቆትን የሚጠየፍ ትውልድ እናፍራ!!!
*******************
ሰዎች ራሳቸውን የሚያኖሩበት የሚንከባከቡበት እና የሚያሳድጉበት ሀብትና ንብረት ማፍራት ይፈልጋሉ፡፡ ስርቆት ደግሞ ሀብትና ንብረት ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የሚቃረን ወይም የሚያመክን ነው፡፡ የራስ ያልሆነውን ወይም የሌላውን ሰው ሀብት፣ ንብረት ፣ ጥቅም ወይም እሴት ሕገ ወጥና ድብቅ በሆነ መንገድ የራስ ማድረግ ኢግብረገባዊ ድርጊት ነው ሲል የአቡነ ጎርጎርዮስ የ11ኛ ክፍል የግብረገብ ትምህርት መማሪያ መጽሐፍ ይገልጻል፡፡
ልጀች ጥሩ የሆነ ግብረገብነት እንዲኖራቸው አንጾ ማሳደግ የወላጅ፣ የመምህራን እና የማህበረሰብን ኃላፊነት የሚጠይቅ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከሚገባው (ከባለ መብት ) ነጥቆ ለራስ ወይም ለማይገባው ማድረግ ከሕግ አንጻር የሚያስጠይቅ ሲሆን ከግብረገብነት አንጻር ደግሞ የሚያስወግዝ ድርጊት ነው፡፡
የለቡ አቡነ ጎርጎርዮስ አንደኛ ደረጃ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት የግብረገብ መምህር የሆኑት ዲ/ን እንዳሻው ተክሉ ልጆችን ስናሳድግ በቅድሚያ የመንግስተ ሰማያት ልጆች እንዲሆኑ አድርገን ማሳደግ ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ መልካም ነገር መስራት የሚችል ቤተክርሰቲያን የሚሄድ እንዲሁም ዘመናዊንም ሆነ መንፈሳዊ እውቀትን አያይዞ የሚጓዝ ነው፡፡
እግዚአብሔር ያላስቀመጥከውን አታንሳ ብሏል፡፡ ስለዚህ ሌብነት ማለት ያላስቀመጥነውን ነገር ማንሳት፣ ያልሰሩበትን መውሰድ፣ ያለፉበትን ነገር ማግኘት ማለት ነው፡፡ ሌብነት ለጊዜው ጥሩ ነገር ያገኘን ወይም የሞላልን ሊመስለን ይችላል እንጂ ትልቁ የሚጎዳን ነገር ሲሆን ውስጣችንን ባዶ ያደርገዋል ያሉት መምህሩ ጨምረውም ሰው ምንም ቢሰራ ምንም ቢያደርግ ከህሊናው ወቀሳ ማምለጥ ስለማይችል ያለፋበትን ነገር ማግኘት ስርቆት እንለዋለን ብለዋል፡፡
ልጆች ሌብነትን መጀመሪያ መጸየፍ ያለባቸው ጉዳቱን በደንብ አውቀው ነው፡፡ የሚሰርቁትንም አካል ማሰብ አለባቸው ትዕዛዙን ነው እሚሰርቁት ያሉት መምህሩ ያላስቀመጥከውን አታንሳ ያለውን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ነው የሚጥሱት ብለዋል፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ከእ/ር ነው የሚሰርቁት ማመን ያለባቸው ያንን ነው፡፡ ከወሰድኩ ከእ/ር ጋር ነው እምጣላው ብለው መወሰን እና ሀሳቡን መረዳት ይኖርባቸዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም ልጆች መጀመሪያ ሌብነትን እንዲጠየፉ ትእዛዙ የእ/ር ነው መስረቅ እ/ርን መስረቅ ነው፣ መዋሸት እ/ርን መዋሸት ነው ሰው ባያየንም እ/ር ግን ያየናል ብለው ማሰብ መቻል እንዲችሉ አድርገን ማሳደግ እንደሚገባ መምህር እንዳሻው ይገልጻሉ፡፡
ልጆች ሲያድጉ በቁመት ብቻ እየገዘፉ መምጣት ሳይሆን በጥበብ፣ በሞገስ እና በራስ መተማመን መሆን ይኖርበታል፡፡ ልጆችን በራስ መተማመናቸውን ከሚያሳጣቸው ነገር አንዱ ደግሞ ሌብነት ነው፡፡ ለጊዜው ደሰተኛ ሊያደርጋቸው ይችላል ነገር ግን በራስ መተማመናቸውን ያሳጣቸዋል ሲሉ መምህሩ ተናግረዋል፡፡
ሌላው ይህ ድርጊት ልጆች ላይ ስነ-ልቦናዊ ቀውስ ያሳድርባቸዋል፡፡ ሁል ጊዜ በፍርሃት እንዲኖሩ ይህ ነገር ተነቅቶብኝስ ቢሆን በማለት እንዲሸበሩ እንደሚያደርጋቸው መምህሩ ሲጠቁሙ ልክ ቃኤል አቤልን እንደገደለው እና ከገደለው በኋላ ከህሊና ወቀሳ ባለማምለጡ ተቅበዝባዥ የሆነውን ለአብነት አንስተዋል፡፡ ስለዚህም ሰውም የራሱ ያልሆነውን ነገር ሲወስድ ሰላም አያገኝም ስነልቦናው ጫና ያሳድርበታል፡፡ በመሆኑም ወጥቶ ወርዶ ማግኘት የሚገባውን ነገር ሰርቆ እና አጭበርብሮ በማግኘቱ ብቻ የውስጥ ሰላም ሲያሳጣ በተጨማሪም በሚሄድባቸው ሁኔታዎች በሚደረጉ ድርጊቶች ማንነቱን እንደሚያሳጣው የግብረገብ መምህሩ ገልጸዋል፡፡
ስለዚህ ልጆችን ስናሳድግ በእያንዳንዱ ነገር ከነርሱ ጋር የሚኖረንን አብሮነት ማዳበር ይኖርብናል፡፡ ልጆች ለሚያደርጉት ነገር መመሰጋገን ቢዳብር አንድ ነገር ወድቆ አንስተው ሲመልሱ ላደረጉት መልካምነት ማመስገን ቢኖር ለነገ ይበልጥ ይበረታታሉ ብለዋል፡፡ እንዲሁም ስሜታዊ ሳንሆን ተገቢ መልስ በመስጠት ስሜታቸውን መጋራት ብንችል ችግርንም መፍታት ያስችላል ብሎም ልጆቻችን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መረዳት እንደሚያስችል የግብረገብ መምህሩ ዲ/ን እንዳሻው ተክሉ ተናግረዋል፡፡
የአቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶችም ልጆች ሌብነትን ተጠይፈው እና በስነምግባር ታንጸው እንዲያድጉ በየቅርንጫፎቹ የተለያዩ የማበረታቻ ድርጊቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል የሰው እቃ አግኝቶ ለመለሰ ተማሪ የስነምግባር አምበሳዳር አድርጎ ስም የመለጠፍ እንዲሁም በተለያዩ ሁኔታዎች የስነምግባር ጉድለትን ለሚያሻሽሉ ተማሪዎች ሰርተፍኬት የመስጠት ልምምድ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የተማሪዎች ግብረገብ መማሪያ መጽሐፉ ልጆችን ወደ ስርቆት የሚገፉ ምክንያቶች በሚል ካስቀመጣቸው መካከል ፍላጎትን መቆጣጠር አለመቻል፣ የጓደኛ ግፊት፣ በቀል እና ስንፍናን ከአለማጥናት ጋር በማያያዝ ለፈተና ስርቆት መዳረግን ያነሳል፡፡ በአጠቃላይ መስረቅ ድርጊቱ በበዛበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሰላምና ደኅንነት፣ መተማመንና መቀራረብ፣ መስማማትና መረዳዳት እንዳይኖር ሲያደርግ የእነዚህ መልካም ነገሮች አለመኖር ደግሞ ለሌሎች እኩይ ነገሮችና ድርጊቶች መንሰራፋት ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡

Scroll to Top