የአቡነ ጎርጎርዮስ የለቡ ሁለተኛ ደረጃ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረውን የዓለም የሴቶች የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ቀንን አስመልክቶ በሀገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ በተመረጡ ሴት ተማሪዎች አማካኝነት ተሳተፈ፡፡
በዕለቱ ከፍተኛ የዘርፉ የመንግስት ባለስልጣናት እና የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 102 ሴት ተማሪዎች በፓናል ውይይቱ ላይ ተሳትፊ ሲሆኑ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ ከ9-12ኛ ክፍል ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል በ10 ሴት ተማሪዎች ተወክሏል፡፡
የፓናል ውይይቱ አላማ ኮምፒውተር እና ሴቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን ሴቶች እንዴት ቴክኖሎጂውን መጠቀም ይኖርባቸዋል፤ ብሎም እድሉ ቢሰጣቸው እና ቢያገኙ በምን አይነት ሁኔታ ጊዜያቸውን ሳያባክኑ ለትምህርታቸው በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ብቻ አተኩረው መጠቀም እንደሚችሉ በስፋት ውይይት የተደረገ ሲሆን በዚህም የሚመለከታቸው አካላት ማለትም ወላጆች፣ መምህራን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡
የቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በፓናል ውይይቱ ንቁ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን በርካታ እውቀቶችን ማግኘት የቻሉበት ብሎም ትልቅ ልምድ የተጋሩበት መድረክ ነው፡፡ እንዲሁም ተማሪዎቹ ከሌሎች ትምህርት ቤት ከመጡ ተሳታፊ ተማሪዎች ጋር የሃሳብ ልውውጥ ያደረጉበት እና ዘላቂ ጓደኝነት የመሰረቱበት ነው፡፡
መምህር ኤልያስ መስፍን ተማሪዎቹ በዚህ መድረክ መሳተፋቸው ወጣ ብለው በተለየ ሁኔታ በሚያገኙት እውቀት ትክክለኛውን ነገር የሚረዱበት ነው ያሉ ሲሆን ከሌሎቹ ተማሪዎች አንፃር ደግሞ እራሳቸውን የሚፈትሹበት ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም ይህንን እድል ማግኘታቸው በራስ መተማመናቸውን ያዳበሩበት እና ከእኩዮቻቸው ጋር ጥሩ የሆነ ተግባቦትን በመፍጠር የተነቃቁበት የአንድ ቀን ቆይታ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ፍሬዘር ገድሉ በበኩላቸው እንደዚህ አይነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚከበር ሁነት ላይ ተማሪዎቹ የመሳተፍ እድል ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳገኙ በመግለጽ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገር ተማሪዎች ጋር ሃሳብ በመለዋወጥ ትልቅ ተሞክሮ ያገኙበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡
ርዕሰ መምህሩ ጨምረውም በቀጣይ በአፍካ ህብረት በኩል ለሚኖሩ ትምህርት ላይ ያተኮሩ ማንኛውም ጉዳዮች ላይ ተማሪዎቻችን ተጋባዥ እንደሚሆኑ ያረጋገጥንበት እና መልካም የሚባል የተግባቦት ስራዎችን የሰራንበት ብሎም ቀጣይነት ያለው ግንኙነት የመሰረትንበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ተሳታፊ ለነበሩ ሁሉም ተማሪዎች የምስክር ወረቀት እና ስጦታዎች በአፍሪካ ህብረት እና በተባባሪ አዘጋጆች አማካኝነት ተበርክቶ መርሃግብሩ ተጠናቋል፡፡
የአክሲዮን ማህበራችንን ድረ ገፅ https://esdros.com/e/ በመከታተል ወቅታዊ መረጃዎችን ያገኛሉ።
