የሲኤምሲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአብይ ፆም የመጀመሪያ ሳምንት ላይ የሰንበት ቁርስ የሚል መርሃግብር በመጀመር በተለያዬ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በእያንዳንዱ ሳምንት ሲጎበኝ ቆይቷል፡፡
ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ መርሃግብሩን ቀጥሎ ባሳለፍነው እሁድ የሆሳዕና እለት መርሃግብሩን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመገኘት በካንሰር በሽታ የተያዙ ታዳጊዎችን ጎብኝቷል፡፡
በመርሃግብሩ ከሁሉም ክፍል የተውጣጡ ተማሪዎች፣ ወላጆች እና የአስተዳደር ሰራተኞች ተሳታፊ ሲሆኑ ተማሪዎቹ ታዳጊዎቹን በማጽናናት እና ምግብ በማብላት ጊዜያቸውን አብረው ማሳለፍ ችለዋል፡፡
ተማሪዎቹ ታዳጊ እኩዮቻቸውን በዚህ መልኩ ሆስፒታል ውስጥ ማግኘታቸው የጤናን ዋጋ የተረዱበት ነው ሲሉ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ዘርይሁን የገለፁ ሲሆን የታማሚ ታዳጊዎች ሁኔታ አሳዛኝ የነበረ ቢሆንም በተማሪዎቹ በመጎብኘታቸው እጅግ ደስተኞች መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መምህሩ ጨምረውም ተማሪዎቹ ሆስፒታሉ ሀገሪቷ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ተካሚዎች መጥተው ድነው የሚሄዱበት ስፍራ ብቻ ሳይሆን ዶክተሮችንም የሚያፈራ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መሆኑን በመመልከታቸው ነገ ዶክተር የመሆን ፍላጎትን ያሰረጹበት እና መነቃቃትን ያገኙበት ነው ብለዋል፡፡
ይህ መርሃግብር በዋናነት በትምህርት ቤቱ ፓርላማ የበጎ አድራጎት ሚንስትር ሃሳብ አቅራቢነት እና ዋና ተዋናይነት ሲከናወን የቆየ ሲሆን ይህንንም ተግባር ስኬታማ እንዲሆን የት/ቤቱ አስተዳደር፣ የወላጅ ኮሚቴዎች እና ወላጆች ፣የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ አካላት እና ተማሪዎች በግንባር ቀደምትነት ጉልህ ሚና ነበራቸው። ተማሪዎቹም ብዙ የህይወት ልምዶችን የተማሩበት እና የታላላቆች ምርቃት ያገኙበት ነበር፡፡
በመጨረሻም ተማሪዎቹ በሆስፒታሉ የነበራቻውን ተዳጊዎችን የመጎብኘት ቆይታ ለታማሚዎቹ እግዚአብሔር ምህረት እንዲሰጣቸው ጸሎት በማድረግ አጠናቀዋል፡፡
