በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስሪ አ.ማ በአቡነ ጎርጎርዮስ ት/ቤቶች መካከል በአዋሬ ቅርንጫፍ ት/ቤት በመገኘት የልምድ ልውውጥ ተካሄደ፡፡
የሁሉም ቅርንጫፍ ት/ቤቶች ርዕሰ መምህራን በተገኙበት የተካሄደው ይህ የልምድ ልውውጥ አጠቃላይ የመማር ማስተማር ሂደትን በተመለከተ የተሻለ አፈጻጸም ያለው ቅርንጫፍ ት/ቤት ለሌሎች ቅርንጫፍ ት/ቤቶች ተሞክሮውን የሚያካፍልበት ነው፡፡
የልምድ ልውውጡ አዘጋጅ ቅርንጫፍ ት/ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ደረጄ በቀለ በቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶቹ የሚገኙት አሰራሮች ምን መልክ አላቸው የሚለውን እንዲሁም የአንድ ቅርንጫፍ ት/ቤት አሰራር ለሌላ ቅርንጫፍ እንደተሞክሮ ለመውሰድ እና ለመተግብር ልምድ የተለዋወጥንበት ብሎም በቀረቡት ሀሳቦች እና ምልከታዎች ላይም የተሰጠንን አስተያየቶች እኛም ተቀብለን የተሻለ አሰራር እንድንከተል እና ት/ቤቱ ጥሩ ቁመና ላይ እንዲገኝ ለማስቻል የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
የማበልጸጊያ ማዕከል፣ ቤተ ሙከራዎች፣ ቤተ መፅሀፍት እና የሰነድ አያያዝ በመስክ ምልከታ ወቅት የተጎበኙ ሲሆን በተማሪዎች የተሰሩ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች፣ የምርምር ውጤቶች እና የስዕል ተሰጥኦ ባላቸው ልጆች የተሳሉ ስዕሎችም ለተሳታፊ ርዕሰ መምህራን ለዕይታ ቀርበዋል፡፡
በትምህር ቤት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ትምህርት ቤቱን የሚጠቅም የፈጠራ ስራዎች እየሰሩ እንደሚገኙ ሆኖም በባለሙያዎች እና በገንዘብ እገዛ ቢደረግላቸው ትልቅ ስራዎችን መስራት እንደሚችሉ አቶ ደረጄ ገልጸዋል፡፡
የልምድ ልውውጡ ተሳታፊ አቶ ጣሳቸው ጫኔ የሰሚት ሁለተኛ ደረጃ ርዕሰ መምህር በተማሪዎች የቀረቡት የፈጠራ ውጤቶች በጣም እንዳስገረማቸው እና ተማሪዎቹ በቴክኖሎጂ ምን ያህል ልቀው መሄድ እንደቻሉ ያየንበት ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ከሳይንሱ ጋር በማጣመር የሰሩትን የምርምር ውጤቶች በማየታችን መልካም ተሞክሮ ያገኘንበት ነበር ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ተሳታፊዎቹ በልምድ ልውውጡ ወቅት የተሰሩ ጠንካራ ስራዎችን ማየት እንደቻሉ፣ ከአንጋፋው ትምህር ቤት ልምድ በመውሰዳቸው ደስተኞች እንደነበሩ እና የተማሪዎቹ የፈጠራ ስራዎች ወደ መሬት ወርደው መሰራት የሚችሉበት ሁኔታ ቢመቻች ሲሉ አስተያየታቸውን በመስጠት በዕለቱ የነበረው መርሀ ግብር ተጠናቋል፡፡
