ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ.

የአቡነ ጎርጎርዮስ ተማሪዎች በፈጠራ ስራዎቻቸው ጎልተው መታየት ችለዋል

ተማሪ መልእክተ ጴጥሮስ የቃሊቲ አቡነ ጎርጎርዮስ አንደኛ ደረጃ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በከተማ ደረጃ በተደረገው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ውድድር ላይ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አሸናፊ መሆን ሲችል ተማሪ አናንያ ባያብል ደግሞ የሰሚት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በሥነ-ህይወት ዘርፍ ሶስተኛ ደረጃን በማግኘት አጠናቋል፡፡
ለሶስት ቀናት በቆየው አውደ ርዕይ በከተማ ደረጃ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች በተሳተፉበት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተማሪ መልእክተ ተፎካካሪ በመሆን በፈጠረው ሮቦቲክ መኪና አድናቆትን በማትረፍ ማሸነፍ ሲችል ተማሪ አናንያ ባያብል ደግሞ በሰራው ባዮ ጋዝ በሥነ-ህይወት ዘርፍ ትምህርት ቤቱን በማስጠራት ከአሸናፊ ተማሪዎች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡
እንደ ተማሪ መልእክተ ገለጻ ሮቦቲክ መኪናው ፊት ለፊት የሚያገኘውን የተዝረከረኩ እቃዎች እራሱን በማንቀሳቀስ እያነሳ ቦታቸው ላይ ማስቀመጥ ይችላል፡፡ እንዲሁም ሥራው የተለያዩ አይነት ጥቅሞችን ጫፉን በመቀያየር እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ደረጃ በተደረገው በዚህ ውድድር ለማሸነፍ ብቻ አይደለም የተወዳደርኩት ማየት የምፈልጋቸውን ነገሮች ማየት ችያለሁ ያለ ሲሆን በዚህም አሁን እየሰራዋቸው ለሚገኙት ሌሎች አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ትልቅ ተስፋን ሰጥቶኛል ብሏል፡፡
ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ ተማሪውን ከመደገፍ አንጻር በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ክብብ በኩል ጊዜ በመስጠት ድጋፍ እያደረገለት እንደሚገኝ እና ለፈጠራ ሥራው ግብአት በሟሟላት እያበረታቱት እንደሚገኙ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ገንዘቤ ገለታ ገልጸዋል፡፡
አቶ ጣሳቸው የሰሚት ሁለተኛ ደረጃ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሲሆኑ ተማሪዎቹ በዚህ ደረጃ ተወዳድረው ማሸነፍ መቻላቸው በጣም ትልቅ መነቃቃትን በትምህርት ቤቱ መፍጠር እንዳስቻለ የገለጹ ሲሆን ለዚህም ውጤት በትምህርት ቤታቸው የሚዘጋጀው ውድድር እራሳቸውን እያሳደጉ እንዲቆዩ በማድረጉ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ የሚሰሩ ሰፊ ፕሮጀክቶች እንዳሉት የገለጸው ተማሪ መልእክተ ሲሆን አሁን ላይ የአውሮፕላን ሙከራ በማድረግ እና የተለያዩ ሶፍትዌሮች ላይ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ብሎም ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ የሚሰጡ ፈጠራዎችን በመስራት ላይ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
ሌላው በአውደ ርዕዩ በተጋባዥ እንግድነት በመታደም የተመልካችን ቀልብ በመግዛት ተጽእኖ መፍጠር የቻለው የሰሚት ሁለተኛ ደረጃ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ዮርዳኖስ ተረጨ ሲሆን በፈጠረው ድሮን ለሶስት ቀናት በቆየው መድረክ ላይ ጎልቶ መታየት ችሏል፡፡
በርካታ ተመልካቾች እና ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች የታደሙበት ይህ አውደ ርዕይ በትምህርት ባለሙያዎች እና በቴክኖሎጂ አዋቂዎች የተዳኘ ነው፡፡

Abunegorgorios

Scroll to Top