ከአቡነ ጎርጎሪዮስ ሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ተማሪዎች የአዲስ አበባ ተግባረእድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን ጎበኙ፡፡
ከሶስት ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡት እነዚህ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የሚማሩትን የፅንሰ ሃሳብ ትምህርቶች በተግባር ለመደገፍ ብሎም ያላቸውን የፈጠራ ሥራ ፍላጎት በተሻለ መልኩ ለማወቅ እና ተግባራዊ እውቀት ለማግኘት የሚያግዝ ጉብኝት አካሂደዋል፡፡
በመሆኑም ኮሌጁ አስራ አንድ የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ከነዚህም መሃከል የእንጨት ሥራ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ የኤሌክትሪክ፣ አውቶ መካኒክ፣ የብረታ ብረት እና የጨርቃ ጨርቅ ሙያዎች የሚጠቀሱ ሲሆን ተማሪዎችም የእያንዳንዱን ትምህርት ክፍል አውደጥናት(workshop) በመጎብኘት ቀላል የማይባል የተግባር እውቀትን ማግኘት ችለዋል፡፡
በኮሌጁ የኢንዱስትሪያል ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ የሆኑት ወ/ሮ አበባ ሽታ ተማሪዎቹ በኮሌጁ የሚገኙትን የትምህርት ክፍሎች መጎብኘታቸው መሰረታዊ ኤሌክትሪክ ምንድነው የሚለውን እውቀት የሚረዱበት እና ምን አደጋ ያስከትላል የሚለውን የሚገነዘቡበት እንዲሁም ምንስ ብፈጥርበት በዚህ መጠቀም እችላለው የሚለውን ተግባራዊ የሆነ እውቀት ያገኙበት ነው ብለዋል፡፡
አሰልጣኟ ጨምረውም በፅንሰ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር እንዲህ መመልከታቸው ሰፊ የሆነ እውቀት እና ተነሳሽነት ማግኘት የሚያስችላቸው ሲሆን በቀጣይም የተሸሉ የፈጠራ ስራዎችን ማበርከት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
ተማሪ ስምኦን ደረጄ የአዋሬ አቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በጉብኝቱ ስለ ቴክኒክ እና ሙያ የበለጠ እውቀት ያገኘውበት ነው ሲል በፅንሰ ሃሳብ ስንማራቸው የነበሩትን ትምህርቶች በተግባር እንዴት እንደምንሰራቸው የተማሩኩበት ነው በዚህም የተለያዩ ማሽኖች እንዴት ነው የሚሰሩት የሚለውን ማየት መቻሌ በቀጣይ የምሰራቸውን የፈጠራ ሥራዎች በተሻለ መልኩ ለመስራት ያስችለኛል ብሏል፡፡
ገሊላ ጌትነት ከሰሚት ቅርንጫፍ የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን በጉብኝቱ ቴክኒክና ሙያ ፈልገን የምንገባበት መሆኑን የተረዳውበት እና የፈጠራ ሥራ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች ደግሞ ወደዚህ መግባታቸው ችሎታቸውን ማዳበር እንዲችሉ የሚያግዝ ቦታ መሆኑን ያየውበት ነው ብሎም በሃገራችን እንደዚህ አይነት የፈጠራ ሥራዎች መሰራት እንደሚችሉ መመልከት መቻሌ ደግሞ ለቀጣይ እንድነቃቃ አድርጎኛል ብላለች፡፡
ከለቡ ቅርንጫፍ የዘጠኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ክብረአብ ሰመረአብ በኮሌጁ የሚገኙ የተለያዩ ሥራዎችን መጎብኘቴ መነቃቃትን የፈጠረብኝ ሲሆን በተለይ የእንጨት ሥራው ትልቁን ድርሻ ሲይዝ በቀጣይ ህይወቴም ላይ ተጽእኖ መፍጠር የቻለ ቆይታን አድርጌያለሁ ብሏል፡፡
ተማሪዎቹ በዘርፉ የሰማኒያ ዓመታት ልምድ ያለውን አንጋፋ ኮሌጅ በመጎብኘታቸው በቆይታቸው ሰፊ የሚባል የተግባር እውቀትን ማግኘት የቻሉ ሲሆን በቀጣይ የሚፈልጉትን የትምህርት ዘርፍ ለመወሰን የሚረዳቸውን ጉብኝት ማድረግ ችለዋል፡፡ ቴክነኪክ እና ሙያ ሰዎች በእጃቸውም በጭንቅላታቸውም መስራት የሚችሉ ሆነው የሚወጡበት ተቋም በመሆኑ ለሃገር ትልቅ አስተዋጽዎ ማበርከት ያስችላቸዋል፡፡