የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች በ2015 ዓ.ም የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 1564 ተማሪዎችን በታላቅ ድምቀት አስመረቁ፡፡
በአዲስ አበባ እና በክፍለ ሀገር በሚገኙ 9 ቅርንጫፍ ት/ቤቶች ሲማሩ የነበሩ ማለትም በአዲስ አበባ በ6 ቅርንጫፎች 1,096 ፣በባሕርዳር 255፣ በወልድያ 80 እና በድሬደዋ 133 በአጠቃላይ 806 ወንድ እና 758 ሴት በድምሩ 1564 ተማሪዎችን አስመርቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኙ ት/ቤቶች የምርቃት መርሐ ግብራቸውን በተለያዩ ቦታዎች ያካሄዱ ሲሆን ሲኤምሲ ቅርንጫፍ በቅድስት ሰአሊተ ምሕረት ቤተክርስቲያን አዳራሽ፣ እግዚአብሔር አብ ቅርንጫፍ በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አዳራሽ፣ለቡ ቅርንጫፍ በማ/ስ/ቅ/ ልደታ ለማርያም እና ደ/መ/መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አዳራሽ ባስመረቁበት ወቅት የየደብሩ አስተዳዳሪ አባቶች በክብር እንግድነት ተገኝተው ተመራቂ ተማሪዎችን ባርከዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የ22 ቅርንጫፍ በየካ ወረዳ 7 ወጣት ማዕከል አዳራሽ፣ ወይራ ቅርንጫፍ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ፣ቃሊቲ ቅርንጫፍ በካፍደም ሲኒማ አዳራሽ አስመርቀዋል፡፡
በክልል ከተሞች ባሕርዳር ቅርንጫፍ በሙሉዓለም አዳራሽ ፣ድሬደዋ ቅርንጫፍ ኢትዮ ጣሊያን ቴክኒክና ሙያ አዳራሽ እንዲሁም ወልድያ ቅርንጫፍ በወልድያ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት አስመርቀዋል፡፡
በምረቃ መርሐግብሩ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የማኔጅመንት አካላት ፣የትምህርት ኤክስፐርቶችን ጨምሮ የቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን፣መምህራን፣ ድጋፍ ሰጪ አካላት፣ የወላጅ ኮሚቴ አባላት፣ የተመራቂ ተማሪዎች ወላጆች እና እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
