ለዳይሬክተሮች ቦርድ ዋና ሰብሳቢ የማዕረግ ስም ተሰጠ

በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ የዳይሬክተሮች ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ለሆኑት አቶ ታደሰ አሰፋ ለቤተ ክርስቲያን እስከ አሁን ላበረከቱት አስተዋጽዎ እና በቀጣይ የሚያበረክቱትን ታሳቢ በማድረግ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የማዕረግ ስም ተሰጣቸው፡፡
ከነሐሴ 29/2014ዓ.ም ጀምሮ መጋቤ ሀብታት ታደሰ አሰፋ የሚል የማዕረግ ስም የተሰጣቸው ሲሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ማደራጃ ማኅበረ ቅዱሳን በልዩ ልዩ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ሀገራዊ ተግባራትን በማበርከት አይተኬ ሚና ስለነበራቸው እና አሁንም ይህንኑ ተግባር እየከወኑ በመሆኑ ይህ ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በመሆኑም አቶ ታደሰ አሰፋ ከቀደሙ አበው እና እመው በቀሰሙትና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባገኙት ዕውቀት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በማገልገላቸው እና አሁንም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባላቸው መንፈሳዊ ክህሎት፣ ዕውቀት እና ሙያ እያገለገሉ ስለሚገኙ ይህ ማዕረግ እንደተሰጣቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስታውቃለች፡፡
በተማሩት ትምህርት፣ ባላቸው መንፈሳዊ ሕይወት፣ ዘመናዊ ዕውቀት እና ትሕትና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን፣ ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ታደሰ አሰፋ እያደረጉ ያሉትን ከፍተኛ አስተዋጽዎ ከግንዛቤ በማስገባት ይህ የማዕረግ ስም ተሰጥቷቸዋል፡፡
ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ የአክስዮን ማኅበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ለሆኑት አቶ ታደሰ አሰፋ ለተሰጣቸው የማዕረግ ስም እንኳን ደስ አሎት በማለት ቀጣይ የአገልግሎት ዘመናቸውን እግዚአብሔር አምላክ ከዚህ በበለጠ የሚተጉበት እንዲያደርግላቸው መልካም ምኞቱን ይገልጻል።

Esdros