በልጆችን አስተዳደግ እና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ስልጠና ተሰጠ፡፡

በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ወይራ ቅድመ መደበኛ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ወላጆች በወላጅ ኮሚቴ አዘጋጅነት “ወላጆች በልጆች አስተዳደግ ላይ ምን መርህ መከተል አለባቸው?” በሚል እና “የልጆች ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ምን መምሰል አለበት” በሚሉ ርዕሳነ ጉዳዮች ላይ ስልጠና ተሰጠ፡፡

Abune Gorgorios

ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በወይራ ቅርንጫፍ መሰብሰቢያ አዳራሽ የተካሄደው ስልጠና የሥነ ልቦና እና የምክር አገልግሎት ባለሙያ በሆኑት ቀሲስ ይግዛው መኮንን እንዲሁም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግር ምክንያት የሚከሰቱ የጎንዮሽ ጉዳት ላይ ያተኮረው ስልጠና ደግሞ በኢንጂነር ሃና የተሰጠ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የስልጠናው ዓላማ ወላጆች ልጆቻቸውን በማሳደግ ሂደት ምን ጉዳዮች ላይ የትኩረት አቅጣቻቸው መሆን እንዳለበት፣ የልጆች ሥነልቦና እና የወላጆች የአዕምሮ ውቅር ቤተክኖሎጂ አጠቃቀም ሊያስከትል የሚችለውን የጎንዮሽ ጉዳትና የሚያድለውን መልካም አጋጣሚ ለማሳየት ያለመ ነው፡፡በተካሄደ የቡድን ውይይት እና በቀረቡ የማጠቃለያ ሃሳቦች ላይ በልጆች አስተዳደግ የወላጆች አካሄድ የተቃኘ ሲሆን የልጆችም ሆኑ የወላጆች በቴክኖሎጂ አግባብ ያልሆነ አጠቃቀም ችግር በልጆች ላይ በወቅቱ ማውራት አለመቻል ፣ መነጫነጭና ሃሳባቸውን መግለጽ አለመቻል ችግር ከማስከተሉ ባሻገር መሠረታዊ የሆኑትን ክህሎቶች አሟልተው እንዳያድጉ በማድረግ ማኅበራዊ ቀውስ ማስከተል ደረጃ መድረሱ በከፍተኛ ደረጃ መወያያ እንደነበር ከቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ ያገኘነው ምረጃ ያመለክታል፡፡
ከ350 በላይ የሚሆኑ ሰልጣኝ ወላጆች በተሳተፉበት ስልጠና ማጠቃላያ ላይ ሃሳባቸውን የሰጡ ወላጆች እንደገለጹት በስልጠናው ሰፊ ዕውቀት እንዳገኙበትና ይህንን መሰል ስልጠና ተጠናክሮ ቢቀጥል የሚል ሃሳብ ተሰቷል፡፡