በወልድያ ቅርንጫፍ የመክፈቻ መርሃ ግብር ተካሄደ

አዲስ በተከፈተው በወልድያ አቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መክፈቻ መርሃ ግብር ተከናወነ፡፡
የመክፈቻ መርሃ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣የሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ኃላፊዎች ፣መጋቤ ጥበባት አክሊለ ብርሃን ተመስገን የወልድያ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ ወላጆች ፣ተማሪዎች ፣ የት/ቤቱ መምህራን እና ሰራተኞች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ሲሆኑ ሰው በሦስት ዕድገቶች ሙሉ ሰው ይሆናል። ይኸውም በአእምሮ ማደግ/የእውቀት ዕድገት/፣ የአካል ዕድገት እና የመንፈስ ዕድገት ናቸው ያሉ ሲሆን በእነዚህ ዕድገት ያደጉ ልጆች አንድ አይና አይሆኑም ሲሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም የሀገር ፣የወገን እና የባልንጀራ ፍቅር ያድርባቸዋል ብለዋል።
እንዲሁም ይህ ዛሬ ሥራውን የጀመረው ትምህርት ቤት መንፈሳዊ እና ሥጋዊ እውቀት የሚያገኙበት በመሆኑ የወላጅ ኮሚቴ ትኩረት ሰጥታችሁ መስራት ይኖርባችኋል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የሆኑት ዲ/ን ፈቃደአብ ሙላው በመርሃ ግብሩ ባደረጉት ንግግር የትምህርት ሥራ በጋራ መከናወን ያለበት በመሆኑ ወላጆች ፣ ተማሪዎች እና መምህራን የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተለያዩ ዝግጅቶች የተከናወኑ ሲሆን በዚህም በአቡነ ጎርጎርዮስ ት/ቤቶች ለቡ ቅርንጫፍ ሲያስተምሩ የነበሩ የግብረ ገብ መምህር የሆኑት መ/ር ዮሴፍ ይልማ ልምዳቸውን አካፍለዋል።
የፀሎተ ማጥንት ሥነ ስርዓት በምድረ ግቢው እና የመማሪያ ክፍሎቹ ውስጥ የተከናወነ ሲሆን በመጨረሻም የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መጀመሩን ማብሰሪያ ችቦ በተማሪዎች ተለኩሶ መከፈቱ ይፋ ተደርጓል፡፡

weldiya