በወልድያ አዲስ ለተከፈተው አቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ሥልጠና ተሰጠ

በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ አዲስ ለተከፈተው ወልድያ አቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ለሚገኙ አዲስ ርእሰ መምህር፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ”Induction and Socialization” በሚል ርዕስ ላይ በወልድያ ከተማ ሥልጠና ተሰጠ፡፡
ሥልጠናው በወልድያ በ2015ዓ.ም አዲስ ለተከፈተው የአቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ሥራ ለሚጀምሩ አዲስ መምህራን፣ ርዕሰ መምህር እና የአስተዳደር ሰራተኞች የተሰጠ ሲሆን የድርጅቱን እሴት፣ ራዕይ፣ ተልዕኮ እና የአሰራር ባህል ማሳወቅ ብሎም የቅድመ ሥራ ሥልጠና እና የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ታሪካዊ ዳራ የሚሉት በሥልጠናው የተካተቱ ርዕሶች ናቸው፡፡
በመሆኑም የአክስዮን ማኅበሩ አደረጃጀት፣ እሴት፣ አላማ እና ተልዕኮ እንዲሁም የአሰራር ባህል በዝርዝር ቀርቧል፡፡ እንዲሁም የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ሙያዊ ሥነ ምግባር ምን ይመስላል፣ የወላጅ አያያዝ እና የድርጅቱን ዕሴት ወደ ማህበረሰቡ እንዴት ማስረጽ እንደሚቻል በሥልጠናው በስፋት ተዳሷል፡፡
ሥልጠናው አዲስ አበባ የሚገኙ የአቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች የአሰራር ሂደቶችን ፣ የተሰሩ በርካታ ተሞክሮዎችን እና ተግባራዊ ክንውኖችን በምስል እና ድምጽ በተደገፈ መልኩ በማሳየት ተግባራዊ ተሞክሮዎችን ማካፈል ያስቻለ ነው፡፡
የቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የሆኑት ዲያቆን ፍቃደአብ ሙላው በሥልጠናው ያላቸውን አስተያየት ሲናገሩ ለአዲስ ቅርንጫፍ የሚያስፈልጉ ሥልጠናዎች በመሰጠታቸው በቀጣይ ለምንሰራቸው ሥራዎች መስፈንጠሪያ ሀሳብ እንደ ርዕሰ መምህር እንዳገኙ በማንሳት ከትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ጋር እና ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን በኔነት ስሜት ለመስራት በቁርጠኝነት እንደተዘጋጁ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱን የተማሪ ወላጆች በመሰብሰብ ጊዚያዊ የወላጅ ኮሚቴ የተቋቋቀመ ሲሆን በዚህም የትምህርት ጥራት የወላጅ ኮሚቴ፣ የትራንስፖርት ወላጅ ኮሚቴ፣ የሥነ ምግባር ወላጅ ኮሚቴ እና ምቹ የትምህርት አካባቢን መፍጠር ላይ ያተኮሩ አራት ኮሚቴዎችን ማቋቋም ተችሏል፡፡ እንዲሁም በቀጣይ የሚሰሩ ሥራዎች ላይ ውይይት በማድረግ በቂ ግንዛቤ ማስረጽ ተችሏል፡፡
የተማሪ ወላጆችም ለአካባቢው ማህበረሰብ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ቢሰራ እና ቀጣይነት ያላቸው ሥልጠናዎች ቢሰጡ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በአጠቃላይ ሥልጠናው ለአርባ አምስት ተሳታፊዎች ለሁለት ቀን የተሰጠ ሲሆን ሰልጣኞች በቆይታቸው የተቋሙን የስራ ባህል፣ ዕሴት፣ ራዕይ እንዲሁም የደንበኞች አገልግሎትን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቂ ግንዛቤ መውሰድ የቻሉበት ነው፡፡