ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ጎበኙ::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ፣ የአዲሰ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች የእግዚአብሔር አብ ቅርንጫፍ ተማሪዎችን ጎበኙ፡፡ብፁዕነታቸው ስለ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የኦርቶዶክሳዊ አገልግሎት እና ተጋድሎ “ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ራሳቸውን አክብረው አባትነትን፣ ሃይማኖተኝነትን፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስከብሩ መሆናቸውን ብዙዎች ይስማሙበታል። የታሪክ ተመራማሪ እንደመሆናቸው በዓለም አቀፋዊነት (ሉላዊነት) መዋጥ እንዳይመጣ ማንነትን ጠብቆ በዓለም መድረክ መገኘትንም አበክረው ያሳስቡ አባት ነበሩ። ሕጻናት ሰብስቦ ማሳደግ የቤተ ክርስቲያን አንዱ ዓላማ መሆኑን በተግባር አሳይተዋል ።ለተተኪው ትውልድ ትልቅ አክብሮት እና ጥንቃቄ በማሳየታቸው ይታወቃሉ። ወጣቶች በዕውቀት እንዲበለጽጉ በብዙ ደክመዋል። ዓላማቸው፣ ጽናታቸው፣ ኢትዮጵያዊ አርበኝነታቸው፣ ለአፍሪካዊነት ያላቸው ከበሬታ፣ ለወላጅ አልባ ሕጻናት ያላቸው አክብሮት ሁሌም የማይረሱ ያደርጋቸዋል።”በማለት አጠር ያለ ትምህርት ሰጥተዋል ፡፡ አያይዘውም የአቡነ ጎርጎርዮስ ት/ቤቶች ለትውልድ እያበረከተ ስላለው አበርክቶት አንስተው አድናቆታቸውን እና ምስጋናቸውን ቅርበዋል፡፡
የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች እግዚአብሔር አብ ቅርንጫፍ ርዕሰ መምህር አቶ የአብሥራም ስለ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ የገለጹ ሲሆን ካለባቸው ሰፊ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ቅድሚያ ልጆቻቸውን ለመጎብኘትና ለመባረክ በመምጣታቸው ከፍተኛ አክብሮትና ምስጋና አቅርበዋል፡፡

 Abune Gorgorios