የብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ እረፍታቸው ተዘከረ

ሐምሌ 22/1982ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ እረፍታቸው በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ ዋና መስሪያ ቤት ሰራተኞች ተዘከረ፡፡
ብዑዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በ1932ዓ.ም ከአቶ ገበየሁ እሰየና ከወ/ሮ አሰለፈች ካሣ በስዕለት በደሴ ከተማ ተወለዱ፡፡ ፊደል የቆጠሩትም በዛው በደሴ መድኃኔዓለም የነበረ ሲሆን ከየኔታ ክፍሌ ( አባ ክፍለ ማርያም) ጋር መገናኘታቸው የሕይወት መስመራቸውን ለውጦታል፡፡
ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በሕጻንነታቸው የኔታ ክፍሌን ተከትለው ከደሴ መድኃኔዓለም ወደ ገነተ ማርያም፣ ከዚያም ወደ ነአኲቶ ለአብና ወደ አባ ቡሩክ ገዳም ትምህርት ፍለጋ እንደሄዱ ታሪካቸው ይናገራል፡፡
በደሴ መድኃኔዓለም ፊደልን መቁጠር የጀመሩት ብጹዕነታቸው በ1963ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት በብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ወደ ግሪክ ተልከዋል፡፡ በደሴተ ፍጥሞ ለሁለት ዓመት መንፈሳዊ ትምህርት ተምረው ዲፕሎማ ከአቴንስ ዩኒቨርስቲ ፣ በሥነ መለኮት የማስትሬት ዲግሪ ከስዊዘርላንድ ፍሪበሪን ዩኒቨርስቲ ፣በፈረንሳይኛ ቋንቋ የምስክር ወረቀት እንዲሁም በኢየሩሳሌም ደብረ ጽዮን የግሪክ መንፈሳዊ ኮሌጅ- በአረብኛ ቋንቋ የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡
ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በነበራቸው ጊዜ በርካታ ሥራዎችን በመስራት ለትውልድ መሰረት መጣል የቻሉ አባት ናቸው፡፡
ሐምሌ 22/1982 ዓ.ም ወደ መቂ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት ሲሄዱ በድንገተኛ የመኪና አደጋ በተወለዱ በሃምሳ ዓመታቸው ሕይወታቸውን ያጡት የወንጌልና የታሪክ ብርሃንን በተለይ በወጣቱ ሕይወት ላይ የፈነጠቁት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ (በድሮው የክፍላተ ሀገር አከፋፈል) የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበሩ።
ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ ከሚያስተዳድራቸው ዘርፎች አንዱ የሆነውን የትምህርት ዘርፍ በእርሳቸው ስም አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች በማለት በመሰየም ታላቅ አባት የነበሩትን ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕን እየዘከራቸው ይኖራል፡፡

 

abunegorgorios