የ2014ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ውይይት ተካሄደ

የኤስድሮስ ኮንስትራክሽን፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ የ2014ዓ.ም የሥራ አመራር አባላት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ውይይት በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ተካሄደ፡፡
የቦርድ አባላት፣ የዋና መሥሪያ ቤት ሥራ አመራሮች እና የትምህርት ቤቶች ርእሰ መምህራን በተገኙበት በቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ የሥራ አፈጻጸሞች ላይ የነበሩ የሥራ ክፍተቶች እና ጠንካራ ጎኖች ላይ ትኩረት በማድረግ ውይይቱ ተካሂዷል፡፡ እንደመነሻ በሁሉም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ የቤተ ሙከራ እና ሌሎች የመማር ማስተማር ግብአቶች ምን ይመስላሉ የሚል ሪፖርት፣ አጠቃላይ የትምህርት ቤቶች ግምገማ እና የተማሪዎች ውጤት ትንተና በማቅረብ ውይይቱ ሊካሄድ ችሏል፡፡
በመሆኑም የአቡነ ጎርጎርዮስ ት/ቤቶች ትምህርትን ለዜጎች ከመስጠት ጎን ለጎን ጥራቱን ለማረጋገጥ የሚረዱ ስልቶችን በመንደፍ በትምህርት ቤቶቹ የመማር ማስተማር ሂደት ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን እየሰራ ይገኛል፡፡ በግብዓት፣ በሂደት እና በውጤት በማሻሻል የተማሪዎችን ውጤት ፣ እውቀት፣ ክህሎት፤ባህሪ እና አመለካከት ከፍ ለማድረግ ቅርንጫፎችን ከላይ በተቀሱት ርእሶች በመመዘን በዕለቱ ሪፖርት ቀርቧል፡፡
በዚህም የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በሁሉም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች በዓመቱ ያጋጠሙ ክፍተቶችን እና ስኬቶችን ተሳታፊዎች ያነሱ ሲሆን ተማሪዎች ጋር ያሉ የመማር ማስተማር ሂደቶች ምን ይመስሉ ነበር፤ እንዲሁም የወላጆችን ፍላጎት ከማርካት አንጻርስ ቆይታችን በምን ሁኔታ ተጠናቋል የሚለውን በማንሳት ለቀጣይ የትምህርት ዘመን እርምቶችን ለመውሰድ ያስችል ዘንድ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ብሎም ከግብአት፣ ከሂደት እና ከውጤት አንጻር በማየት ለየቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶቹ በግምገማ ደረጃ መስጠት እንደቻለ በዕለቱ ተገልጿል፡፡ የክልል ቅርንጫፎችን ጨምሮ የሁሉም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች የዓመቱ የሥራ ሁኔታ በዝርዝር በቀረበበት በዚህ መድረክ ያጋጠሙ ችግሮች እና የተወሰዱ መፍትሄዎችን በማቅረብ መማሪያ ማድረግ ተችሏል፡፡
በአጠቃላይ በዓመት ውስጥ በሁሉም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች የነበረው የስራ አፈጻጸም በውይይቱ ሲዳሰስ ፤የነበሩ ክፍተቶችን አርሞ ለመቀጠል ብሎም የተመዘገቡ ጠንካራ ጎኖችን ለመጠበቅ በሚያስችል መልኩ ውይይቱ ተካሂዷል፡፡
በመጨረሻም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት በተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሃሳብ የሰጡ ሲሆን፤ በቀጣይ ዓመት መስተካከል የሚገባቸው ነገሮችን ትኩረት በመስጠት ሲናገሩ የተሰሩ መልካም ሥራዎች ደግሞ እንዲቀጥሉ አበረታተዋል፡፡ እንዲሁም ለቀጣይ ዓመት የትምህርት ዘመን በተሻለ አፈጻጸም ለመሄድ ያስችል ዘንድ ቦርዱ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የእለቱ ውይይት ተጠናቋል፡፡