የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በዛሬው ዕለት ተጀመረ

የአቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች የ2015ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመክፈቻ መርሃ ግብር በሁሉም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች ወላጆች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የቦርድ አባላት እና የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በድምቀት ተካሄደ፡፡
ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶቹ የመክፈቻ መርሃ ግብሩን በተለያዩ ዝግጅቶች ያስጀመሩ ሲሆን በዚህም በሁሉም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች የመክፈቻ ንግግር በተጋባዥ እንግዶች እና ርዕሰ መምህራን ተደርጓል፡፡
ትምህርት የሰዎች ሁለንተናዊ ስብዕና የሚቀረፅበት ሂደት እና የአንድ ሃገር ሰብዓዊ ሀብት የሚገነባበት መሣሪያ ነው። በዚህ ረገድ የሰብዓዊ ሀብት በተፈጥሮ ሀብት ላይ ካለው የበላይነት የተነሣ ትምህርት የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት መሆኑ በመክፈቻው መልዕክት ተገልጿል፡፡
እንዲሁም ተማሪዎች ከዛሬዋ ቀን ጀምሮ ትምህርት ቤታቸውን የሚጠብቁ፣ የሚጠበቅባቸውን ተግባራት ሁሉ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ቃል የሚገቡበት ዕለት በመሆኑ ቃላቸውን ጠብቀው ለነገ ሀገር እና ቤተክርስቲያን ተረካቢ ትውልድ ለመሆን እንዲዘጋጁ፤ በጉዟቸው ደግሞ መምህራን እና ወላጆች በጋራ በመሥራት አኩሪ ትውልድ መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው በመክፈቻው ንግግር ተላልፏል፡፡
በሁሉም ቅርንጫፎች በተመሳሳይ ሰዓት በተካሄደው በዚህ የመክፈቻ መርሃ ግብር ስለ ትምህርት ቤቱ አሰራር መግለጫ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም በ2014ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን ለሌሎች ተማሪዎችም ተሞክሮአቸውን አካፍለዋል፡፡
በዛሬው ዕለት በተጀመረው የትምህርት ዘመን በሁሉም የአቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች የተማሪ እና ወላጅ ግንኙነት ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ የተሰራ ሲሆን በተጨማሪም ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው ከእነርሱ የሚጠበቁትን ተግባራት እና በትምህርታቸው ማስመዝገብ ስለሚገባቸው ውጤቶች ላይ ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል፡፡
በመሆኑም አዲሱን የትምህርት ዘመን እንዴት ማሳለፍ እንደሚጠበቅባቸው እና በከፍተኛ ትጋት ትምህርታቸውን መከታተል እንደሚገባ ሲገለጽ በእውቀት የበለጸጉ እና በሥነ ምግባር የታነፁ ልጆች መሆን ይገባቸዋል ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች በ2015 ዓ.ም ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በመክፈት እና የተማሪ ቅበላ አቅሙን በማሳደግ በቅድመ አንደኛ፣ በአንደኛ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በ24 ቅርንጫፎች ከ17,000 በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ የእግዚአብሔር አብ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤትም በዚህ ዓመት አዲስ ከተከፈቱት ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደማቅ የሆነ የመክፈቻ ዝግጅት በማከናወን ጉዞውን ጀምሯል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ የፀሎተ ማጥንት ሥነ ስርዓት ተከናውኗል፡፡

 

Esdros