ሰው አክባሪ ትውልድ እናፍራ!!!
ግብረገብነት እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች ሰዎች እና ከራሱ ሕይወትና እድገት፣ መብትና ነፃነት፣ ጥቅምና ፍላጎት፣ ክብርና ዓላማ አንፃር ማድረግ የሚገባው ወይም ማድረግ የማይገባው ድርጊት መሆን የሚገባው ጠባይ ወይም መሆን የማይገባው ጠባይ ነው ሲል የአቡነ ጎርጎሪዮስ ት/ቤቶች የግብረገብ ትምህርት መማሪያ መፅሀፍ ይገልፃል፡፡
ታዲያ ግብረገብነት መገለጫዎቹ በርካታ ኢትዮጵዊ እሴትን የያዙ ድርጊቶች ሲሆኑ ከነዚህ መሀከል አንዱ ሰው አክባሪነት ነው፡፡ ሰው ክቡር ፍጡር ነው፡፡ ልጆችም ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲያድጉ ኢትዮጵዊ እሴትን በማወቅ እና በመተግበር የሰውን ክቡርነት በመረዳት እንዲያድጉ የቤተሰብ፣ የመምህራን እና የማህበረሰብ ኃላፊነት ነው፡፡
ሰውን ማክበር በርካታ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን ልጆች በልጅነታቸው እያወቋቸው ማደግ ከሚገቡ የሰው አክባሪነት ድርጊት መገለጫዎች መሀከል የታላላቆችን ትእዛዝ ማክበር ፣ ወላጆችን ማክበር፣ ለታላላቆች የመቀመጫ ቦታ መልቀቅ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ተከባብረው እና ተሳስበው ጊዜያቸውን ማሰለፍ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ሆኖም ልጆች አድገው ነገ ሰው አክባሪ ይሆኑ ዘንድ ፍሬውን መዝራት እና በተገቢው ሁኔታ ማሳደግ መጀመር የሚኖርብን በልጅነት እድሜያቸው ላይ ነው፡፡
የአቡነ ጎርጎርዮስ ት/ቤቶችም ይህንን ሀገራዊ ሀላፊነት በመረዳት በስነምግባር የታነፀ ትውልድን ለመገንባት ወላጆች ልጆቻቸውን በስነምግባር አንፆ ማሳደግ ከሚኖርባቸው ኃላፊነት ጎን ለጎን ለተማሪዎቹ የግብረገብ ትምህርት ማስተማሪያ መጽሀፍትን በማዘጋጀት እያስተማረ ይገኛል፡፡
በትምህርት ዘርፍ ሱፐርቫይዘር የሆኑት አቶ ማስተዋል ጌጤ ሰውን ማክበር ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት ማለት ነው። በዚህም ተማሪዎቻችን ግቢ ውስጥ ሲገቡ ከጥበቃ ጀምረው ከመምህራኖቻቸው ጋር እንዲሁም ከጓደኞቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት በየዕለቱ የሚተገብሩት ጉዳይ ነው ብለዋል።
አንድ ተማሪ ሳይንሱን ብቻ እንዲያውቅ አይደለም የምናስተምረው ያሉት ሱፐርቫይዘሩ በዕውቀት፣ በክህሎት እና በስብዕናም ጭምር የጎለበቱ ተማሪዎች እንዲሆኑ እየተሰራ ነው። በመሆኑም እውቀት ከትህትና ጋር አብሮ ሲመጣ ውጤታማ ይሆናል ብለዋል።
የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች የግብረገብ ትምህርት ነገ ልጆች አድገው በሚያደርጓቸው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ አሻራ ማሳረፍ ሲችል ለሀገርም በስነምግባር የታነፁ ብቁ ዜጎችን ለማበርከት ያስችላል፡፡

