ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ የመንፈሳዊ ጉዞ መርሃግብር አካሄደ

በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ የአቡነ ጎርጎርዮስ ሲኤምሲ የመጀመሪያ ደረጃ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ወደ ገዋሳ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ወአቡነ ሀብተማርያም ገዳም መንፈሳዊ ጉዞ በማድረግ የተለያዩ መርሃግብሮችን አካሄደ፡፡
የወላጅ ተማሪ መምህራን ህብረት(ወተመህ) የትምህርት ቤት ሥነ-ምግባር ዘርፍ ባዘጋጀው በዚህ መርሃግብር ላይ ወላጆች፣መምህራን፣ የዋና መስሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች፣ የትምህርት ቤቱ የተማሪዎች የፓርላማ አባላት እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችም ታድመዋል፡፡
በዕለቱ የተለያዩ ዝግጆች የቀረቡ ሲሆን በመምህር ገ/እግዚብሔር እና በመ/ር መስፍን ክርስቲያናዊ የልጆች አስተዳደግ እና ኢትዮጵዊ እሴት ላይ እንዲሁም ተጨማሪ የማነቃቂያ ስልጠና ለወላጆች ተሰጥቷል፡፡ የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት እንዴት ተግዳሮቶችን መቋቋም ይቻላል ብሎም ወደ ስራ አለም ሲገቡ ያላቸውን ባህሪ እና የሚገጥማቸውን ተግዳሮት በተመለከተም ተሞክሮአቸውን ለሌሎች አካፍለዋል፡፡
በተጨማሪም ገዳሙ እንዴት ተቋቋመ የሚለው ከታሪካዊ አመሰራረቱ ጀምሮ ለተጓዦች ገለጻ እየተደረገ ጉብኝት የተካሄደ ሲሆን በተማሪዎች የቀረቡ ልዩ ልዩ መነባንቦች፣ ዝማሬዎች እና የበገና ድርደራዎችም የመርሃ ግብሩ አካል ነበሩ፡፡
የቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ዘርይሁን አንዳንድ ተማሪዎች ላይ የሥነ-ምግባር ጉድለት በመኖሩ ወላጆች በልጆች አስተዳደግ ላይ ትክክል ያልሆነ ነገር እንዳያደርጉ ለማስተማር እና ልጆቻቸው ላይ ክትትል ለማድረግ የሚያግዝ ስልጠና ነው ብለዋል፡፡ አንድ እጅ ብቻውን ማጨብጨብ አይችልም ያሉት ርዕሰ መምህሩ የወላጆች እገዛ እጅግ ስለሚያስፈልግ ስልጠናው ተዘጋጅቷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ የሥነ-ምግባር እና በጎ አድራጎት ክበብ አባል ተማሪዎች የወላጆችን እጅ የማስታጠብ ሥራ በማከናወን ለበጎ አድራጎት ስራ የሚውል 6ሺ ብር መሰብሰብ ችለዋል፡፡
በአጠቃላይ ወላጆች በስልጠናው እና በነበረው መርሃግብር እጅግ ደስተኞች እንደሆኑ በመግለጽ እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች በአመት ሁለት ጊዜ መሰጠት ቢችሉ ብለዋል፡፡