በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ ለወላጆች እና አሳዳጊዎች ስልጠና ተሰጠ

በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ወይራ ቅርንጫፍ በልጆች አስተዳደግ እና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለወላጆች እና አሳዳጊዎች ስልጠና ተሰጠ፡፡

ስልጠናው ወላጆች/አሳዳጊዎች ስለልጆቻቸው ማወቅ ስለሚኖርባቸው ዋና ዋና ነገሮች ላይ እንዲሁም ልምዶቻቸውን  እንዴት ለልጆቻቸው ማካፈል እንደሚኖርባቸው ብሎም ልጆች በእድሜያቸው የሚያጋጥማቸውን  የተለያዩ ተግዳሮቶች እንዲቋቋሙ ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው እና ተጨማሪ በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ ያሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ልጆች እድሜቸው እየጨመረ ሲመጣ ከሚያመጡት የተፈጥሮ እና የባህሪ ለውጥ አንጻር ወላጆች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎች (መገናኛ ብዙሀን እና ማህበራዊ ሚዲያዎች) ልጆች  ላይ እያስከተሉ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ እና እንዴት መጠቀም ይኖርባቸዋል የሚሉት በስልጠናው ላይ ተነስተው ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ የመጀመሪያ ደረጃ ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ አክሊለ አሜጋ  ስልጠናው ልምድ ባላቸው አሰልጣኞች የተሰጠ መሆኑን ገልጸው ወላጆች በልጆቻቸው ትምህርት እና ፀባይ ላይ ያተኮረ ስልጠና መሆኑ ወላጆች ያለባቸውን ኃላፊነት በደንብ ከስልጠና መድረኩ የተረዱበት ነበር ብለዋል፡፡

ልጆች እሴቶቻችንን እና ኢትዮጵያዊ ትውፊቶቻችንን ጠብቀው ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዴት ማስተላለፍ እንደሚኖርባቸው እንዲሁም የልጆች አስተዳደግ ካለንበት ወቅት እና ዘመን አንጻር እንዴት  መቃኘት እንደሚኖርበት  በስልጠናው ላይ  በስፋት ውይይት ተደርጎበታል፡፡

አቶ ኤፍሬም  ስሜ በስልጠናው ላይ ከተገኙ የተማሪ ወላጆች  መካከል አንዱ ሲሆኑ  ስልጠናው ወቅቱን ያገናዘበ ስልጠና ነው ያሉ ሲሆን ወላጅ ምን ያህሉን ኃላፊነቱን ተወጥቶ ነው ለት/ቤቱ ኃላፊነትን ሰጥቶ የሚቀመጠው የሚለውን በደንብ ያየንበት እና ወላጅ ላይ ብዙ የቤት ስራ እንዳለ እንደ መንፈሳዊ እና አትየጵያዊ ወላጅ ያለብንን ኃላፊነት የተገነዘብንበት ነው ብለዋል፡፡

እንዲሁም በተግባር ምሳሌዎች እየተነሱ የሰለጠንበት ስልጠና በመሆኑ ብዙ ልምድ ያገኘንበት ነው፡፡ ብሎም ልጆች የእግዚያብሔር ስጦታዎች በመሆናቸው የኛን ኃላፊነቶች በደንብ የተረዳንበት እና በአግባቡ መወጣት እንዳለብን የተገነዘብንበት ነው ሲሉ አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች በሌሎች ቅርንጫፍ ት/ቤቶችም የሚሰጥበት ሁኔታ ቢመቻች እና ተጠናክሮ ቢቀጠል ሲባል በመድረኩ ተጠቁመል፡፡