በድሬደዋ እና ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች ሥልጠና ተሰጠ

በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ በሰው ሀብት አስተዳደር መምሪያ አማካኝነት በድሬደዋ እና ባሕር ዳር አቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች የአመለካካት ለውጥን ለማሳደግ የሚያስችል ሥልጠና ተሰጠ፡፡
ሥልጠናው የነበረን አመለካከት ለማሳደግ ፣አስተሳሰብን ወደ ተግባር የመለወጥ ቁርጠኝነት ላይ እንዲሁም የለውጥ አስተዳደር ላይ ትኩረት አድረጎ የተሰጠ ሲሆን በዚህም በሥራ እና በግል ሕይወት ብሎም በእምነት እውቀትን በማስፋት፤ እይታ እና አመለካከትን በማሻሻል እንዴት ወደ ስኬት መምጣት ይቻላል የሚለው ግንዛቤ የተሰጠበት ርዕስ ነው፡፡
በተጨማሪም እምነት ካለ፤ የውስጥ መሻት ልክ ከሆነ እና ጥረት ከተደረገ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በሥልጠናው የተጠቀሰ ሲሆን ዘመኑ የሚፈልገው እውቀት፣ እይታ እና አመለካከት ሊኖር እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
ልክ የሆነውን በመስራት ችግር ፈቺ እና ውጤት አምጭ ባለ ራዕይ መሆን ፤ አዳዲስ አስተሳሰቦች እንዲገነቡ ማድረግ፤ በጋራ በመሆን አዳዲስ ነገሮችን ማምጣት እና የመጨረሻውን ትልቁን ህልም ማሰብ እና የምንፈልገውን ለውጥ ለማምጣት ብቃትን መጨመር አስፈላጊ እንደሆነ በድሬደዋ በነበረው የሥልጠና መድረክ ተጠቅሷል፡፡
አመለካከት በየዕለቱ በህይወታችን የምናየው እና በሚገጥሙን ነገሮች የምንፈጥረው እይታ ነው የተባለው ደግሞ በባሕር ዳር በነበረው የሥልጠና መድረክ ላይ ሲሆን አንድ ነገር በራሱ መጥፎም ጥሩም እንዳልሆነ ነገር ግን የምንቀበልበት መንገድ መጥፎ ወይም ጥሩ ያደርገዋል ተብሏል፡፡
በሁለቱም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች ለሁለት ቀናት በተሰጠው ሥልጠና ሰልጣኞች በነበራቸው ቆይታ እጅግ እንደተደሰቱ እና የወሰዱት ሥልጠና ከሥራ ባሻገር ለህይወታቸው ጠቃሚ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን የባሕር ዳር አንደኛ ደረጃ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ነብዩ በላይ ሥልጠናው የሁሉንም ምልከታ ወደ አንድ ያመጣ ነው በማለት ተቋሙ ይህን ሥልጠና መስጠቱ በጣም ትልቅ መነሳሳትን፣ ሀይል እና ጉልበትን ብሎም አንድነትን መፍጠር አስችሎታል ብለዋል፡፡
የድሬደዋ አንደኛ ደረጃ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ም/ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ሊቀመንበር መንግስቱ ሥልጠናው ጥሩ እና ገንቢ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን በተለይ ስብእና ግንባታ ላይ አተኩሮ መሰጠቱ አይምሮአዊ ለውጥን ማምጣት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም ይህ አይነቱ ሥልጠና ምን ደረጃ ላይ ነው ያለውት በማለት እራስን መገምገም የሚያስችል በመሆኑ ቀጣይነት ቢኖረው ሲሉ ተናግረዋል፡በአጠቃላይ ከክረምት ጀምሮ በተካሄደ መርሃ ግብር 1096 በቅርንጫፍ የሚገኙ ባለሙያዎች በተለያዩ የሥልጠና ዘርፎች ማሰልጠን የተቻለ ሲሆን በዚህ ዙር በባሕር ዳር እና ድሬደዋ በድምሩ 231 ባለሙያዎች ሰልጥነዋል፡፡ በቀጣይ ለዋናው መስሪያ ቤት ሰራተኞች ሥልጠናው እንደሚሰጥ ከሰው ሃብት አስተዳደር መምሪያ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡