አክስዮን ማህበሩ ለዋና መስሪያ ቤት አመራሮች ስልጠና ሰጠ
ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አክስዮን ማህበር ለዋና መስሪያ ቤት አመራሮች እና ቡድን መሪዎች በስልታዊ አመራር ዙሪያ ስልጠና ሰጠ፡፡
በስልጠናው ቅን መሪ መሆን ፣ ውሳኔ ሰጭነት፣ ድርጅታዊ አቅም ፣ የአመራር ደረጃዎች፣ በራዕይ መምራት እና ጥልቅ እሳቤ የመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች በስፋት ተዳሰዋል፡፡
ውጤታማ መሪ ቅንነት እና አቅም ሲመጣጠኑ የሚመጣ ነው ያሉት በዕለቱ ስልጠናውን የሰጡት አቶ ትዛዙ ይሁኔ ሲሆኑ መሪ አዳዲስ ዕይታዎችን የሚያይ ከመቆጣጠር ይልቅ ለስራ የሚያነሳሳ እና የሚመራ ነው ያሉ ሲሆን በራዕይ መምራት ደግሞ ዋናው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ አንድ መሪ በራዕይ ሲመራ አርቆ አሳቢነት ፣ አሻግሮ ማየት እና ትልቅ እይታን ይላበሳል ሲሉ በስልጠናው አንስተዋል፡፡
ስልታዊ አመራር ሁለት ነገርን የሚይዝ ነው ይህም በትልቁ ማሰብ በትልቁ መተግበር ፤ በሩቅ ማሰብ እና በጊዜ መተግበር እንዲሁም አሻግሮ ማየት እና የነገውን አልሞ ዛሬ መስራት እና ማቀድን እንደሚያካትት አቶ ትዛዙ ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው ለድርጅቱ አመራሮች መሰጠቱ ዕይታቸውን እንዲያስተካክሉ፣ በትልቁ እንዲያስቡ፣ አሻግረው እንዲያዩ እና በጥልቀት ማሰብ ለመጀመር አማራጭ መንገዶችን እንዲያዩ ብሎም የነገውን የተቋሙን አቅጣጫ በጥሩ መንገድ ለማስቀመጥ እና ትክክለኛውን መንገድ እንዲቀይሱ እጅግ አጋዥ እና ጠቃሚ ነው ሲሉ አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡
አቶ ነጋ ሞላው የሎጀስቲክ እና ንብረት አስተዳደር መምሪያ ስራ አስኪያጅ ስልጠናውን ከወሰዱት አመራሮች መካከል አንዱ ሲሆኑ ስልጠናውን በተመለከተ ስልጠና ራስን ለማሻሻል የሚረዳ ነው፡፡ ራሳችንን እንድናይ፣ አዳዲስ ነገሮችን እንድንመለከት እና እንድንገመግም ይረዳል ያሉ ሲሆን የዛሬውም ስልጠና እንደ አመራር ተመሳሳይ የሆነ ችሎታ ላይ እንድንደርስ ያደርገናል ይህም ማለት አንዳንድ ጊዜ የሆነ አካል ወደ ኋላ ሊቀር ይችላል እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች የማቀራረብ፣ የማመሳሰል አንድ አይነት ቋንቋ እንድንናገር የማድረግ አቅም ስለሚኖራቸው በጣም ጥሩ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ነጋ ጨምረውም የድርጅታችንን የ5 ዓመት እቅድ እየከለስን ባለንበት ወቅት ይህን ስልጠና መውሰዳችን ግምገማችንን ሰፋ አድርገን እንድናይ እንዲሁም ዕይታችን ሰፋ እንዲል ያደርጋል ብለዋል፡፡ ሌላው እኛ ብቻ ሳንሆን የቡድን አስተባባሪዎችም ይህንን ስልጠና መውሰዳቸው በስራ ላይ የሚኖረንን ተግባቦት ጥሩ ያርገዋል ሲሉ ተናግዋል፡፡ በተጨማሪም ስልጠናውን የድርጅቱን አላማ የተረዳ ሰው መስጠቱ የቱ ጋር ትኩረት ማድረግ እንዳለበት በደንብ ስለሚረዳ እና ተግባራዊ የሆኑ ከእኛ ስራ ጋር የተያያዙ ምሳሌዎችን እየሰጠን ማሰልጠኑ ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች ቀጣይነት ቢኖራቸው አመራሮችን ብቻ ሳይሆን ሰራተኞችም ማሰልጠን ቢቻል ስራ በቡድን የሚሰራ በመሆኑ ውጤታማ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ጥሩ ርዕሰ ጉዳዮች ቢነሱም የነበረው ጊዜ እጅግ አጭር ነበር እንዲሁም በቀጣይ የስልጠና ቦታ ከቢሮ ወጣ ብሎ ቢመቻች ሀሳብን ሰብስቦ ለመሰልጠን ምቹ ያደርገዋል ሲሉ ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
በዕለቱ ስልጠናውን የሰጡት አቶ ትዛዙ ይሁኔ በፋይናንስ እና በቢዝነስ አስተደዳር ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በዘርፉ ባለራዕይ መሪ እና ቅን መሪ የሚሉ ሁለት መፅሀፍቶችን ያበረከቱ ናቸው፡፡ የተስተካከለ ዕይታ ካለ የተስተካከለ አሰራር እና አካሄድ ይኖራል፡፡ ዓለም የውድድር ናት ተወዳዳሪዎችን አሸንፎ ደግሞ ተቋሙን ወደተሻለ መንገድ ለመውሰድ ይህ ስልጠና ስለሚረዳ ለአመራሮች መሰጠቱ ወሳኝ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡