አክስዮን ማኅበሩ ለዋናው መ/ቤት ሰራተኞች ሥልጠና ሰጠ

ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ ለዋና መስሪያ ቤት ሰራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ ሆቴል ሥልጠና ሰጠ፡፡
ሥልጠናው የአመለካከት ለውጥን ለማሳደግ እና የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥን የተሻለ ማድረግ ያስችል ዘንድ ‘Attitude Skills for Success at Work in Life’ እና ‘customer service in an organization’ የደንበኞች አገልግሎት በድርጅት ውስጥ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተሰጥቷል፡፡
በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር የቦርድ አባል በሆኑት በዶ/ር ቀጸላ ኃይሉ የተደረገ ሲሆን የድርጅቱን ዓላማ ለማሳካት ጠንክሮ መስራት ተገቢ ነው በማለት ትውልድን የመቅረጽ ሥራ ስለምንሰራ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ትውልድን በሥነ ምግባር አንጾ ለማሳደግ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ጨምረውም ሠልጣኞች ሥልጠናውን ትኩረት ሰጥተው በመከታተል ወደ ተግባር ማምጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የአክስዮን ማኅበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል በሆኑት በወ/ሮ እንዬ ቢምር በደንበኞች አገልግሎት ላይ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ ጥሩ የሆነ ተግባቦት ከደንበኞቻችን፣ ከተማሪዎቻችን እና ከወላጆች ጋር መመስረት እና የተሻለ አመራር መፍጠር መቻል ተገቢ ነው በማለት ደንበኞች እና ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል በልዩነት ሊያስታውሰው የሚችል ተቋም መገንባት ደግሞ በእጅጉ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ሥልጠናው ተሳታፊዎቹ ተገቢ የሆነ አመለካከት፣ ዕውቀትን እና ክህሎትን እንዲጨብጡ በማድረግ በሥራቸው እና በአኗኗራቸው የዘይቤ ለውጥ እንዲያመጡ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
አሁን ያለውን አመለካከት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ያስችል ዘንድ ‘Attitude Skills for Success at Work in Life’ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሥልጠና የሰጡት ደግሞ በሥራ አመራር ዘርፍ የተመሰከረላቸው አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አሸናፊ አበራ ሲሆኑ በሥልጠናቸውም በህይወት የራስ ዕቅድ እንደሚያስፈልግ እና ዕቅዱን ለማሳካት መኖር መጀመር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ህይወታችንን አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ የማድረግ አቅም ውስጣችን እንደሚገኝ በምሳሌ አስረድተዋል፡፡
ለእያንዳንዱ የተቋም ግንባታ ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ አስተዋጽዎ እንዳለው በሥልጠናው የተጠቀሰ ሲሆን ለውጥ የሚመጣው ደግሞ ኃላፊነት መውሰድ ሲቻል ነው ተብሏል፡፡
ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹን አነጋግረን ከሰጡት አስተያት መረዳት እንደተቻለው፤ በነበራቸው ቆይታ በጣም እንደተደሰቱ እና ለሥራም ሆነ ለህይወት እጅግ ጠቃሚ ሥልጠና እንዳገኙ በማንሳት እንዲህ አይነቱ ሥልጠና ወላጆችን እና ተማሪዎችን ማሠልጠን ብንችል የተሻለ አመለካት እና ተግባቦት መፍጠር ያስችለናል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በሥልጠናው ላይ በመገኘት የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የአክስዮን ማኅበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ዋና ሰብሳቢ የሆኑት መጋቤ ሀብታት ታደሰ አሰፋ ሲሆኑ በንግግራቸውም “በሕይወት መልካሙንም ክፉውንም ለማድረግ ተፈቅዶልናል ይህ ደግሞ የኛ ምርጫ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ መልካሙን ማድረግ ከቻልን መልካም ይሆናል ብለዋል፡፡ ጨምረውም ራሳችንን ይበልጥ ልናበቃበት የምንችልበትን መንገድ ከዚህ ሥልጠና በመነሳት ያለውን ክፍተት በመለየት መስራት መቻል ይጠበቅባችኋል ሲሉ ለሥልጠናው ተሳታፊዎች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ እንዲሁም የቦርድ ሰብሳቢው ሥልጠናው እንዲሳካ ያደረጉትትን የድርጅቱን የሥራ ኃለፊዎች፣ የሰው ሀብት አስተዳደርን፣ ሥልጠናውን የሰጡ አካላትን እና የሥልጠናው ተሳታፊዎችን አመስግነዋል፡፡
ሥልጠናው የድርጅቱን የአመራር እና የሠራተኛ ብቃት በማሳደግ የደንበኞችን እርካታ ከፍ ለማድረግ ያግዝ ዘንድ የተዘጋጀ ሲሆን አመለካከትን ወይም አስተሳሰብን ወደ ላቀ ከፍታ ለማሸጋገር ተጨባጭ ምሳሌዎችን በማንሳት የተሰጠ ነው፡፡