አክስዮን ማኅበሩ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሥልጠና ሰጠ
ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ የሰው ሀብት አስተዳደር መምሪያ ከትምህርት ሚንስተር ጋር በመተባባር በአቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ የሒሳብ እና ሳይንስ መምህራን በትምህርት ሚንስቴር ሳይንስ እና ሥነ ጥበባት ማበልፀጊያ ዴስክ ሥልጠና ሰጠ፡፡
ሥልጠናው ለሳይንስ እና ሒሳብ መምህራን የተሰጠ ሲሆን “በአክቲቭ ለርኒግ፣ አሰስመንት ፎር ለርኒግ፣ ፕራክቲካል ላቦራቶሪ፣ ሌሰን ፕላኒግ አና ሌሰን ስተዲ” በተሰኙ ርእሶች ላይ በማተኮር በተግባራዊ ማሳያዎች ተደግፎ የተሰጠ ነው፡፡
በሥልጠናው የመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት የአክስዮን ማኅበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ዋና ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ታደሰ አሰፋ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም አክስዮን ማኅበሩ ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት የቦታ ተግዳሮት ቢኖርበትም፤ ይህንን ችግር ተቋቁሞ በቀጣይ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ላይ ቅርንጫፎችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ በማንሳት በዚህም መልካም ዜጎችን የማፍራት ርዕዩን ለማሳካት የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ጨምረውም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና የትምህርት ጥራትና ቁጥጥር ባለሥልጣን እንዲሁም የክልል ከተሞች ትምህርት መምሪያዎች እየሰጡን ያለው ድጋፍ የሚያበረታታ ስለሆነ ለማመስገን እወዳለሁ ሲሉ በንግግራቸው ገልጸዋል፡፡
የዳይሬክተሮች ቦርድ ዋና ሰብሳቢው ሠልጣኞችን በተመለከተ የወሰዳችሁትን ሥልጠና ወደ ተሰማራችሁበት ቅርንጫፍ ስትመለሱ ተግባራዊ ከማድረግ ባሻገር ለሌሎች መምህራን ማሰልጠን ይኖርባችኋል ሲሉ ለመምህራኑ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
ዶ/ር ሙሉቀን ንጋቱ በኢፌድሪ የትምህርት ሚንስቴር የመምህራን እና ትምህርት አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚ በዕለቱ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ ሥልጠናውን የተከታተላችሁ መምህራን በቆይታችሁ ያገኛችሁትን እውቀት ሌሎችን በማሰልጠን እነርሱን ማብቃት መቻል ይኖርባችኋል ሲሉ አደራ ብለዋል፡፡ እንዲሁም ትምህርት ሚንስቴር ባዘጋጀው በዚህ የሥልጠና መርሃ ግብር የመጀመሪያው በመሆናችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት ለመምህራኑ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አቶ የሰውዘር በላይነህ በትምህርት ሚንስቴር የትምህርት ሚንስትሩ አማካሪ ሲሆኑ በመዝጊያው መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ሚንስቴሩ እናንተን ለማገዝ ጥረት እና ዝግጅት ሁልጊዜም ያደርጋል ያሉ ሲሆን እናንተም በተግባር ያገኛችሁትን ሥልጠና የፈጠራ ሥራ በማከል በተግባር መስራት ይኖርባችኋል በማለት በጥሩ ሥነ ምግባር ሥልጠናችሁን በማጠናቀቃችሁ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
ለሒሳብ እና ሳይንስ ( ለኬሚስትሪ፣ ለባይሎጂ፣ እና ለፊዘክስ) መምህራን በተሰጠው በዚህ ሥልጠና ላይ ተሳታፊ የነበረችው መምህርት ምንታምር ምህረተ በሲኤምሲ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት የኬሚስትሪ መምህር ስትሆን ሥልጠናውን በተመለከተ በሰጠችው አስተያየት አካባቢያችን ላይ ካሉት ነገሮች እንዴት የማስተማሪያ ቁሳቁሶችን እንደምንሰራ በተግባር ተምረናል፤ ያለች ሲሆን ዕቅድን በተመለከተም ለይምሰል ከሚሆን ይልቅ የምር አስበን አቅደን ብንገባ ለተማሪዎቹም ሆነ ለመማር ማስተማር ሂደቱ ጥሩ እንደሚሆን ተረድቼበታለሁ ስትል ሀሳቧን ገልጻለች፡፡
በሁሉም ርእሶች ላይ በተግባር የተደገፈ ሥልጠናን ባካተተው በዚህ መርሃ ገብር ተሳታፊ የነበረው መምህር መንግስቱ ታደሰ በወይራ ቅርንጫፍ የፊዚክስ መምህር ሲሆን ሥልጠናው በንድፈ ሀሳብ ብቻ አስተምረን የምናልፈውን ትምህርት እንዴት በቀላሉ አካባቢያችን ላይ ከምናገኛቸው ቁሶች ለተግባራዊ ትምህርት የሚያግዙ ነገሮችን ሰርተን መጠቀም እንደምንችል ግንዛቤ ያገኘውበት ነው ብሏል፡፡
ሥልጠናው ለአምስት ቀናት ለሰባ ዘጠኝ(79) የሳይንስ እና ሂሳብ መምህራን በተግባራዊ ልምምዶች ተደግፎ የተሰጠ ሲሆን ትምህርት ሚንስቴር ከላይ በተጠቀሱት ርዕሶች የአክስዮን ማኅበሩ የሳይንስ እና ሒሳብ መምህራን ሥልጠናውን በስኬት ማጠናቀቃቸውን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ለድርጅቱ አበርክቷል፡፡ እንዲሁም ተሳታፊዎች ሥልጠናውን ተከታትለው ማጠናቀቃቸውን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት የአክስዮን ማኅበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ከሆኑት አቶ ታደሰ አሰፋ ተቀብለዋል፡፡