አክስዮን ማኅበሩ የትውውቅ እና የሥልጠና መርሃ ግብር አካሄደ

በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ነባር፣ አዲስ እና ሰልጣኝ መምህራን ብሎም ለአስተዳደር ሰራተኞች በአዋሬ የአቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት የትውውቅ እና የሥልጠና መርሃ ግብር አካሄደ፡፡
ሥልጠናው አክስዮን ማኅበሩ በ2015ዓ.ም አዲስ ለሚከፍተው ለእግዚአብሔር አብ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ለተቀጠሩ ነባር፣አዲስ እና ሰልጣኝ መምህራን ብሎም የአስተዳደር ሰራተኞች የተሰጠ ሲሆን በዚህም በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ተዳሰዋል፡፡
በሥራ ላይ መኖር ስለሚገባ አመለካከት እና ሙያዊ ሥነ ምግባር፣ የአክስዮን ማኅበሩ አደረጃጀት፣ ራዕይ፣ ተልኮ እና የድርጅቱ የስራ ባህል ምን ይመስላል የሚለው ላይ ትኩረት በማድረግ ሰልጣኞቹ የሚቀላቀሉትን ድርጅት እሴት አስቀድመው መገንዘብ በሚችሉበት ሁኔታ ሥልጠናው ተሰጥቷል፡፡
በዕለቱ የዲቮትድ ኮንሰልቲንግ ባለቤት የሆኑት አቶ ሙላት መብራቴ በሥልጠናው መጀመሪያ ላይ ገለጻ በማድረግ የድርጅታቸው የሥራ አመራር አማካሪ የሆኑትን ዶ/ር ዮሴፍ ውብዓለምን ለስኬታማ ሥራ መኖር ስለሚገባ አመለካከት (Attitude skills for success at work) ላይ ሥልጠና እንዲሰጡ የጋበዙ ሲሆን በዚህም ዶ/ር ዮሴፍ ትክክለኛውን አመለካከት አንድ ሰራተኛ ከያዘ የማገልገል ባህሪ ፣የተቋም ታማኝነት እና እርስ በእርስ ከሰራተኞች ጋር የሚኖረው ግንኙነት በአጠቃላይ ታክለውበት እውቀት እና ክህሎቱ ተጨምሮ ብቃቱን በትክክል ትርጉም ሊሰጥ በሚችልበት መንገድ ያውለዋል ብለዋል፡፡
ባለሙያነት እና የንግድ ስራ ሥነ ምግባር (professionalism and business ethics) ላይ ያተኮረ ሥልጠና ደግሞ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል በሆኑት በወ/ሮ እንዬ ቢምር የተሰጠ ሲሆን ሰልጣኞቹ ለትምህርት ቤቱ ጥሩ የሚሆኑት እራሳቸው ለመለወጥ ዝግጁ ከሆኑ እና ችግሮችን እየፈቱ መሄድ ሲችሉ ነው ይህም ደግሞ በብዙ ሰዎች ዘንድ ድርጅቱ ተመራጭ እንዲሆን እድል ይፈጥራል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የተቋሙን አጠቃላይ አደረጃጀት እና የሰው ሀብት አስተዳዳር መመሪያን ብሎም የተቋሙን እሴቶች በተመለከተ ሰልጣኞች ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ በአክስዮን ማኅበሩ የሰው ሀብት አስተዳደር መምሪያ ሥራ አስኪያጅ በሆኑት በአቶ ዘሪሁን አድማሱ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን በአክስዮን ማኀበሩ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ(በትምህርት ዘርፍ) በሆኑት አቶ ዘሪሁን ክብርት ደግሞ የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶችን ታሪካዊ ዳራ፣ ራዕይ፣ ተልእኮ እና አጠቃላይ በትምህርት ዘርፍ የሚገኙ አሰራሮችን ከመንግስት መመሪያዎች ጋር በመቃኘት ለሰልጣኞች ግንዛቤ መፍጠር ያስቻለ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡
ሥልጠናውን ለሁለት ቀናት የተከታተሉት መምህራን በቆይታቸው በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ እና የድርጅቱን አጠቃላይ ባህል የተረዱበት ብሎም የወሰዱት ሥልጠና የግል ህይወታቸውን መለወጥ የሚያስችላቸው ጭምር እንደሆነ በማንሳት በቀጣይም ተጠናክሮ ቢቀጥል ሲሉ አስተያየታቸውን በመስጠት የሚጣልባቸውንም ኃላፊነት በአግባበቡ እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
የአክስዮን ማኅበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ዋና ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ታደሰ አሰፋ በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ በመገኘት ሰልጣኞቹን እንኳን ወደ ተቋማችን ተቀላቀላችሁ በማለት የመዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በመልእክታቸውም የተቋሙ ራዕይ፣ ተልዕኮ እና እሴቶች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡ እንዲሁም ተቋሙን ተቀላቅላችሁ ስራ በምትጀምሩበት ጊዜ የድርጅቱን እሴቶች በመጠበቅ እና በማስጠበቅ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ትውልድን የሚተካ ትውልድ ማፍራት ይኖርባችኋል ብለዋል፡፡
ጨምረውም መምህርነት የተከበረ ሙያ ነው ሙያችሁን እያሳደጋችሁ መሄድ ይኖርባችኋል እንዲሁም ተቋሙን የራሳችሁ አድርጋችሁ በመቁጠር ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ሲሉ ለመምህራኑ አስገንዝበዋል፡፡
ሥልጠናው ለስልሳ መምህራን የተሰጠ ሲሆን ሰልጣኞች በቆይታቸው የተቋሙን የስራ ባህል እና እሴት የተረዱበት ከመሆኑ ባሻገር ሙያቸውን አክብረው እና አዳብረው ለመዝለቅ ትልቅ ግብአት ያገኙበት ነው፡፡