አክስዮን ማኅበሩ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት አካሄደ
ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን እና ስልታዊ ዕቅዱን መነሻ በማድረግ በተዘጋጀው የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የቦርድ አባላት እና የድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በኢንተርኮንትነታል ሆቴል ውይይት አካሂዷል ፡፡
በመሆኑም በውይይቱ ላይ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ የነበሩ ክፍተቶችን በማየት የ2015 ዓ.ም ዋና ዋና ዕቅዶችን በስፋት ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ በዚህም የበጀት ዓመቱ ዕቅዶች በዝርዝር የዕቅድ ዝግጅት ክትትል እና ግምገማ ከፍተኛ ባለሙያ በሆኑት በአቶ እንዳለ ተሾመ የቀረቡ ሲሆን በዕቅድ አፈጻጸም ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን እና መልካም አጋጣሚዎችንም በማስቀመጥ ዕቅዱ ለውይይት ቀርቧል፡፡
በዚህም በቀረበው የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የቦርዱ አባላት እና የሥራ ኃላፊዎች ውይይት ያደረጉ ሲሆን የቦርድ አባላቱ በቀረበው ዕቅድ ላይ አስተያየት በመስጠት መስተካከል የሚኖርባቸው እና ያልተካተቱ መካተት ይገባቸዋል የሚሉትን ጉዳዮች ጠቁመዋል፡፡
ቅድሚያ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በትኩረት ማየት እንደሚገባ ብሎም በቀጣይ በሚኖሩ ሥራዎች እና ዕቅዶች ላይ በደንብ መረጃ እና ጥናት የሚፈልጉትን ጊዜ ወስዶ ጥናት ማድረግ ተገቢ እንደሆነ በውይይቱ ላይ የቦርድ አባላቱ አንስተዋል፡፡
በውይይት መድረኩ በአጠቃላይ የሥራ ኃላፊዎች ከባለፉት ዓመታት በተሻለ መልኩ እታች ድረስ በመውረድ ክፍተቶችን ማየት እንዳለባቸው እና የሚፈጠሩ ችግሮችንም በፍጥነት እየቀረፉ መሄድ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በዕለቱ ካለፈው በጀት ዓመት አፈጸጸም በመነሳት የቀጣዩን ዓመት አካሄድ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የተሞከረ ሲሆን የቦርድ ዋና ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ታደሰ አሰፋ ግምገማችን ትልቅ የትምህርት ጊዜ ነበር በማለት ቆይታቸው ፍሬያማ እንደነበር በማንሳት የተሰጡትን አስተያየቶች እንደግብዓት በመውሰድ አቅማችንን በደንብ ተጠቅመን ስጋት የሚባለውን ቀንሰን መሄድ ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም አሁን ያሉንን መልካም ነገሮች በተሻለ ሁኔታ ይዞ መጓዝ ተገቢ እንደሆነ ዋና ሰብሳቢው በንግግራቸው አንስተዋል፡፡
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ዕቅድ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በዚህም መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች ተስተካክለው እና መጨመር የሚኖርባቸው ጉዳዮች በተሰጡት አተያየቶች መሰረት ተካተው የሚቀጥል ይሆናል፡፡