ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ ከአሐዱ ባንክ ጋር ተፈራረመ
በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ እና በአሐዱ ባንክ መካከል የጋራ ሥራ ስምምነት ፊርማ በአሐዱ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ተደረገ፡፡
የመግባቢያው ስምምነት በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ. ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አንተነህ ፈለቀ እና በአሐዱ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በአቶ ሰፊዓለም ሊበን መካከል ተደርጓል፡፡
በዚህም የመግባቢያ ስምምነት የኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ ቋሚ ሰራተኞች የቤት መግዣና መስሪያ ብድር፣ መኪና መግዣ እንዲሁም ለግል አገልግሎት የሚሆን ብድር ከባንኩ እንዲያገኙ የሚያስችል ይሆናል፡፡
በዚህ በጋራ ለመስራት በተደረገው ስምምነት የኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ በባንኩ በኩል የባንክ አገልግሎትን እንዲፈጽም ከስምምነት የተደረሰ ሲሆን ባንኩም ለቤት መግዣ ብድር እስከ 25 ዓመት የሚቆይ ብድር እና አንድ አመት የብድር መክፈያ እፎይታ ጊዜን የሰጠ ሲሆን ለቤት መስሪያ ብድር እስከ 25ዓመት የሚቆይ ብድር እና እስከ 2 ዓመት ድረስ የብድር መክፈያ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን በተደረሰው ስምምነት ተካቷል፡፡
ለመንቀሳቀሻ መኪና መግዣ ብድር የተሸከርካሪው የስሪት ዓመት ከ10 ዓመት ያልበለጠ ሆኖ የብድር መክፈያው ጊዜም በ10 ዓመት ውስጥ ተፈጻሚ የሚሆን ብድርም የተካተተበት ነው፡፡ ሠራተኛው ለግል አገልግሎት እስከ 700 ሺህ ብር ብድር መበደር የሚችል ሲሆን የብድሩ መክፈያ የጊዜ ወሰን እስከ 3 ዓመት የሚቆይ መሆኑን ከስምምነት ሰነዱ ያገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ1600 በላይ ሠራተኞች ያሉት ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ የሠራተኛውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ ባንኮች ጋር ስምምነቶችን በመፈጸም በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡
የአክሲዮን ማህበራችንን ድረ ገፅ https://esdros.com/e/ በመከታተል ወቅታዊ መረጃዎችን ያገኛሉ።