ውሸት

ሰው ሰብአዊ ፍጡር ሆኖ መኖርና ማደግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያለ ግብረገብ  የኖረበት ጊዜ የለም ፡፡ ይህ ማለት ለሰው ህይወት የሚበጅ የግብረገብ መሰረታዊ መርህ ፍለጋ ከጥንት ጀምሮ ነበረ፡፡

ፍለጋው ዛሬም ቢሆን ቀጥሏል፡፡ ምክንያቱም ብዙ የተባሉ ነገሮች  ቢኖሩም  ሁሉኑም የሚያስማማ መርህ ዛሬም የተገኘ አይመስልም፡፡ እውነተኛ ችግሩ ግን ሁሉኑም የሚያስማማ መርህ መታጣት አይደለም፡፡ ይልቁንም ሰው በተፈለገው መንገድ ራሱን ሁለንተናዊ ለሆኑ ግብረገባዊ መርሆች ማስገዛት አለመቻሉ ነው ሲል የአቡነ ጎርጎርዮስ የግብረገብ  መማሪያ መጽሀፍ ይገልጻል፡፡

የሰው ልጅ ትክክል የሆነውን ድርጊት የመፈጸም ትክክል ያልሆነውን ድርጊት ያለመፈጸም ግብረገባዊ ግዴታ አለው፡፡ ሁሌም ግብረገባዊ ግዴታችንን በሚገባ የምናከናውን ከሆነ ባህሪያችን ሰናይ ምግባር የተላበሰ ነው፡፡ በተቃራኒው ግብረገባዊ ግዴታችንን የማናከናውን  ከሆነ ባህሪያችን በእኩይ  ምግባር  የተበከለ ነው ሲል የአቡነ ጎርጎርዮስ የግብረገብ መጽሀፍ ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡

ታዲያ ልጆች በአስተዳደጋቸው ወቅት በእኩይ ምግባር የተበከለ ባህሪ እንዳይኖራቸው  ከልጅነት ጀምሮ ሰናይ ምግባሮችን  እያስተማርናቸው እና እያለማመድን እንዲያድጉ ማድረግ የወላጅ፣ የማህበረሰብ እና የመምህራን  ኃላፊነት ነው፡፡

እኩይ ከሆኑ በርካታ ምግባሮች መሀከል እንዱ ውሸት መዋሸት ነው፡፡ መዋሸት ማለት እውነትን ማዛባት ነው፡፡ መዋሸት በተዛባ መረጃ የሰዎችን አስተሳሰብ መቀየር ነው፡፡

መምህር ፈቀደ ሽሙ በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች የግብረገብ እና የግዕዝ መምህር  ልጆች ውሸት ማውራታቸው ይጎዳቸዋል ሲሉ ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን ልጆች ባዶ ወረቀት ናቸው እንደሚባለው ማንም  ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማው ቃል ነው ወደ አይምሮው የሚመጣው ይህም  ውሸትን በተደጋጋሚ የሚሰሙ ከሆነ እውነት የሚመስልበት ሁኔታ ይኖራል ብለዋል፡፡

ወላጆች/አሳዳጊዎች ልጆቻቸውን በሚያሳድጉበት ወቅት ውሸት በልጆች ፊት መናገር አይኖርባቸውም፡፡ ልጆች የሚያዩትን ነው የሚያንጸባርቁት ያሉት መ/ር ፈቀደ ጨምረውም ልጆች መዋሸታቸው ወይም ውሸትን መለማመዳቸው ጓደኛቸውን ሊያሳጣቸው ይችላል፣ ታማኝነትን ያሳጣል ብሎም ሀገርንም  እስከ ማፍረስ እና ትውልድንም ሆነ ቤተሰብን ሊጎዳ ስለሚችል መዘዙ ብዙ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶችም የግብረገብ ትምህርት ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በሁሉም የክፍል ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎቹ እያስተማረ ይገኛል፡፡ እንደ መ/ር ፈቀደ ገለፃ ልጆች ከህጻንነታቸው ጀመረው ስነምግባር መማራቸው በህጻንነት የተማሩት ትምህርት አይሬሰነት ስላለው በቀጣይ ህይወታቸው ላይ በጎ ተፅአኖ እየፈጠረ እስከ እድሜ ልካቸው የሚኖር ነው ብለዋል፡፡ ታዲያ ይህ የህይወት ስንቅ ድጋፍ ሆኖአቸው ከሌሎቹ ትምህርቶች ጋር ጎን ለጎን ለማስኬድ እንደሚያስችላቸው ይገልጻሉ፡፡

ልጆችን መዋሸት እንደሌለባቸው እየተናገርን ብናሳድጋቸው የስነምግባር በጎ ገጽታ  ነው፡፡ አለመዋሸት ታማኝነትን  እና በጎነትን ስለሚገልጽ ትልቅ ጥቅም ይሰጣቸዋል፡፡ ልጆች በመዋሸታቸው ወይም ውሸትን በመለማመዳቸው ስብእናቸው የተዛበ ይሆናል፡፡ እውነት እና ውሸት በሚለዩበት እድሜ በመታረሚያ ጊዜያቸው እርምት ካልተሰጣቸው ውሸታም የሚል ስብእና ይዘው ያድጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ በእድገታቸው ላይም ውሸታም መባላቸው በራስ መተማመናቸውን ይቀንሳል፡፡

በአጠቃላይ ልጆቻችንን በምናሳድግበት ጊዜ በራስ መተማመን እንዲኖራቸው፣ መዋሸታቸው በሚፈጥርባቸው የመጸጸት ስሜት ስነ ልቦናዊ የሆነ ጉዳት እንዳይገጥማቸው እና ድንጉጥ ስብእና እንዳይላበሱ ከጅምሩ ኃላፊነታችንን መወጣት አንዘንጋ፡፡