ዝክረ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ተካሄደ

Esdros S.C, [8/1/2023 2:26 PM]
[ Album ]
ዝክረ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ተካሄደ
******************** ******************** ********************
ሐምሌ 22/1982 ዓ.ም በድንገተኛ የመኪና አደጋ ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ እረፍት በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ ማኔጅመንት እና ሠራተኞች ተዘክሯል፡፡
በታላቁ አባት በብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የእረፍት መታሰቢያ ዝግጅት ላይም ዋኖቻችሁን አስቡ በሚል ኃይለቃል ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲሆን የብጹዕነታቸው የሕይወት ታሪክ እና ሥራዎች በሰፊው ተዳሰዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር በዕለቱ የብጹዕነታቸውን ሕይወት ከውልደት እስከ እረፍት የሚያወሳ ሥነ-ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን በዚህም በ1932ዓ.ም ከአቶ ገበየሁ እሰየና ከወ/ሮ አሰለፈች ካሣ በስእለት በደሴ ከተማ መወለዳቸው፣ በደሴ መድኃኔዓለም ፊደልን መቁጠር መጀመራቸው፣ በ1963ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት በብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ወደ ግሪክ መላካቸው፣በደሴተ ፍጥሞ ለሁለት ዓመት መንፈሳዊ ትምህርት ተምረው ዲፕሎማ፣ ከአቴንስ ዩኒቨርስቲ በሥነ መለኮት የማስትሬት ዲግሪ፣ ከስዊዘርላንድ ፍሪበሪን ዩኒቨርስቲ በፈረንሳይኛ ቋንቋ የምስክር ወረቀት እንዲሁም በኢየሩሳሌም ደብረ ጽዮን የግሪክ መንፈሳዊ ኮሌጅ- በአረብኛ ቋንቋ የምስክር ወረቀት ማግኘታቸው ተወስቷል፡፡

Esdros S.C, [8/1/2023 2:26 PM]
በመርሐ ግብሩ ላይ ከተወሳው የብጹዕነታቸው ታሪክ አስገራሚው ብጹዕነታቸው በኢየሩሳሌም እያሉ አንድ ቀን ሌሊት ከተኙበት ክፍል አንድ ቀላ ያለ ረጅም ሰው ቀስቅሷቸው አሁን በዚህ የምትቀመጥበት ጊዜ አይደለም፤ ወንጌል ለማስተማር ወደ ኢትዮጵያ እንሂድ ይላቸዋል፡፡ በትእዛዙ ግራ በመጋባት ማንነቱን ሲጠይቁት ኤፍሬም ሶርያዊ ነኝ ይላቸዋል፡፡ ከዛም ጠዋት ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጥሪ ደረሳቸው፡፡ በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ኤጲስ ቆጶስ ዘሸዋ ተብለው ተሾሙ፡፡
ብጹዕነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ የመተዳደሪያ ደንብ አዘጋጅተው እንዲጸድቅ ማድረግ የቻሉ ታላቅ ሊቅ ሲሆኑ ለካህናት ማሠልጠኛ ሥርዓተ ትምህርት ቀርጸው፡ የመማሪያና ማስተማሪያ ጥራዝ አዘጋጅተው ያስተምሩ ነበር፡፡ በዝዋይ ሐመረ ብርሃን በመሠረቱት የቅዱስ ገብርኤል ገዳም የዕውቀት ዓምባ አቋቁመው ኢትዮጵያዊውን ታሪክ ከዓለሙ ጋር እያነጻጸሩ ለደቀመዛሙርቶቻቸው ያስተመሩም ነበር። ለገዳማውያኑና ለትምህርት ከየከተማው ለሚሰባሰቡት ተማሪዎቻቸው ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ለተማሪዎቹ ዕውቀትና ሥነ ልቡና በሚመጥን መልኩ ሲያቀርቡ መስማት ያስደንቅ ነበር። ለትምህርት ወደ ዝዋይ የሚመጣ በበጀት እጥረት አይመለስም ነበር፡፡ በክረምት መኝታ ቤት ሞልቶ በድንኳን እያደሩ የሚማሩ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ብዙዎች ከዝዋይ መለየት አቅቷቸው በዚያው ቀርተዋል፡፡

የሃይማኖትና የታሪክ ጥናትና ምርምራቸውን “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” እና “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ” በሚሰኙ መጻሕፍቶቻቸው ቅልብጭ አድርገው አቅርበዋል።
በ1980 ዓ.ም. 12 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ተቀብለው በክረምት መርሐ ግብር ማስተማር የጀመሩት ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ለዛሬው የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበራት መስፋፋት መሠረት መጣላቸው በመርሐግብሩ ላይ ተወስቷል፡፡
ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በነበሯቸው 10 የጵጵስና ዓመታት በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ለትውልድ መሠረት መጣል የቻሉ አባት እንደሆኑ በመርሐግብሩ ላይ ተወስቷል፡፡
ሐምሌ 22/1982 ዓ.ም በድንገተኛ የመኪና አደጋ በተወለዱ በሃምሳ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ሕይወታቸውን ያጡት ታሪክን እና የወንጌልን ብርሃን በወጣቱ ሕይወት ላይ ለመፈነጠቅ ወደ መቂ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት ሲፋጠኑ መሆኑን ታሪካቸው ያወሳል፡፡
ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ በስማቸው በተሰየመው አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ታሪካቸውን እምነታቸውንና ለሀገርና ለቤተክርስቲያን የነበራቸውን ራእይ ለትውልዱ እያሳወቀ ዘወትር ብጹዕነታቸውን ሲዘክራቸው ይኖራል፡፡
የብፁዕ አባታችን በረከት ይደርብን!
የአክሲዮን ማህበራችንን ድረ ገፅ https://esdros.com/e/ በመከታተል ወቅታዊ መረጃዎችን ያገኛሉ።

 

Abune Gorgorious

በተያያዘ ዜና
የብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የእረፍት ቀን መታሰሰቢያ ዝግጅት በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ተዘጋጅቷል፡፡
በመርሀ ግብሩም ላይ ካህናት አባቶች ፀሎተ ወንጌል እና ማዕጠንተ ዕጣን የተደረሰ ሲሆን በተማሪዎች እና በመምህራን የብፁዕነታቸው ታሪክ ተወስቷል፡፡ የተለያዩ ዝማሬዎች እና መጣጥፎችም ቀርበዋል፡፡
ብፁዕ አባታችን ከሚታወቁባቸው ኃይለ ቃል አንዱ “ዝም ብለህ ስራህን ሥራ” የሚለው መልዕክተ ቃል ሙሉ በሙሉ ተነቦ የመርሀግብሩ ፍፃሜ ሆኗል፡፡
በመርሀግብሩም ላይም የአቧሬ ቅርንጫፍ የክረምት ተማሪዎች ፣መምህራን እና ወላጆች ተገኝተው ተካፍለዋል።

 

Abune Gorgorious