የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የኢ-ለርኒንግ የመማር ማስተማር ስራን ጀመሩ
በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን፣ ንግድና ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የኢ-ለርኒንግ የመማር ማስተማር ስራ መጀመራቸው ተገለፀ፡፡
ትምህርት ቤቶቹ በአለም አቀፍ ብሎም በሀገር ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የገፅ ለገፅ ትምህርት መንግስት ባወጣው መመሪያ መሰረት በፈረቃ እያከናወኑ ሲሆን ይህንንም ለማገዝ ያመች ዘንድ የኢ-ለርኒንግ የመማር ማስተማር ስራን ዛሬ ጀምረዋል፡፡
የአክሲዮን ማህበሩ የትምህርት ዘርፍ ተወካይ አቶ ዘሪሁን ክብረት እንደገለፁት ተማሪዎች በቤታቸው በሚሆኑባቸው የትምህርት ቀናት ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ታስቦ የተዘጋጀው የኢ-ለርኒንግ የመማር ማስተማር ስራ ከአፀደ ህፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች በተመጠነ መንገድ ይሰጣል፡፡
ያለምንም የጊዜና የቦታ ገደብ የትምህርት ይዘቶችን ጥራትና አግባብነት በማሻሻል በጥራትና በብቃት ትምህርትን ለማድረስ ያስችላል የተባለለት ኢ-ለርኒንግ፤ ምዘናን ወጥነት ባለው መንገድ ተግባራዊ ከማድረጉም በላይ የክፍል ውስጥ መማር ማስተማርን እንደሚደግፍ አቶ ዘሪሁን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ቴክኖሎጂው ከትምህርት ቤቶቹ የትምህርት አሰጣጥ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ መዘጋጀቱን ያብራሩት አቶ ዘሪሁን ትምህርቱን ለመስጠት መሰረታዊ ግብዓት የሚሆኑ ማዕከላዊ ማስታወሻዎች፣ መለማመጃ ጥያቄዎችና ሙከራዎች፣ የትምህርት ገለፃ ቪዲዮዎች፣ ለዲጂታል ቤተመፅሀፍት የሚያገለግሉ መፅሀፍት እና ሌሎችም ተዘጋጅተው ወደመጀመሪያ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል፡፡
ወላጆች ትምህርቱን በተገቢው መንገድ ለተማሪዎች ለማድረስ አቅም በፈቀደ መጠን የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን እንዲያዘጋጁ፣ ከት/ቤቶቹ የሚወጡ መመሪያዎችን መነሻ በማድረግ የአጠቃቀም እውቀት እንዲይዙና ተማሪዎችም ለትምህርቱ የሚውሉ መገልገያዎችን ላልተፈለገ አላማ እንዳይጠቀሙ ክትትል እንዲያደርጉ ኃላፊው አሳስበዋል፡፡
ትምህርቱን ከዛሬ ህዳር 29 ቀን ጀምሮ elearning.esdros.com ላይ በመግባት ማግኘት እንደሚቻልም ተገልጿል፡፡
ኢ-ለርኒንግ የመማር ማስተማር ስራ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ማለትም ኮምፒዩተር፣ ስማርት ስልኮች፣ ታብሌቶችና አይፎኖችን ከኢንተርኔት አገልግሎት ጋር በማገናኘት ለተማሪዎች ትምህርትን ማድረስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡
የአክሲዮን ማህበራችንን ድህረ ገፅ https://esdros.com/e/ እና የቴሌግራም ቻናል https://t.me/Esdrossc ይከታተሉ፡፡