የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የገፅ ለገፅ ማስተማር ስራቸውን ጀመሩ

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የገፅ ለገፅ ማስተማር ስራቸውን ትናንት በይፋ ጀምረዋል፡፡
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ለወራት ተቋርጦ የነበረው የገፅ ለገፅ ትምህርት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ከህዳር 21 ቀን ጀምሮ መሰጠት እንዲጀምር የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርቱን መስጠት ጀምረዋል፡፡

ትምህርት ቤቶቹ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ትምህርቱን የጀመሩ ሲሆን የትምህርት ቤቶቹ ማህበረሰብ እና ተማሪዎች ወረርሽኙን ለመከላከል የተቀመጡ ፕሮቶኮሎችን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡

የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የሲኤምሲ ቅርንጫፍ ርዕሰ መምህር አቶ እስክንድር ገመቹ በትምህርት መክፈቻ ስነስርዐቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ዘመቻ የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀው በትምህርት ቤቱ የተቀመጡ ህጎችን በማክበር ጤናቸውን እንዲጠብቁም አሳስበዋል፡፡

የትምህርት ቤቱ አስተዳደር የተማሪዎችን ተጋላጭነት ለመከላከል ግብዓቶችን ከማሟላት ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የተቀመጡ የወረርሽኝ መከላከያ ፕሮቶኮሎችን ተግባራዊ እያደረገ ስለመሆኑ የገለፁት አቶ እስክንድር፤ ትምህርቱ ከስጋት ነፃ በሆነ መንገድ እንዲሰጥ ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች ከጥቅምት 16 ቀን ጀምሮ ለስምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ተፈታኞች ትምህርት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ትናንት እና ዛሬ ደግሞ ሞዴል ፈተናዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ፤ የፊታችን ህዳር 24 እና 25 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ ትምህርት ቢሮ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ክልል አቀፍ ፈተናቸውን የሚወስዱ ይሆናል፡፡

በአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ስራው የተሳለጠና የተቀመጠለትን ግብ ይመታ ዘንድ በሁሉም ቅርንጫፎች የሚሰሩ መምህራን የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡