የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ላይ ያደረገውን የዳሰሳ ጥናት ግኝት መነሻ በማድረግ ለ2015 ዓ.ም ተፈታኞች ዋናውን የሀገር አቀፍ ፈተና አምሳያ (ሲሙሌሽን) የሞዴል ፈተናን የሰጠበትን ሂደት እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ አነሳሽ ምክንያቶችን እንቃኛለን፡፡

በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በየዩኒቨርሲቲዎች በመመደብ የሀገር አቀፍ ፈተናውን እንዲወስዱ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ይህን ተከትሎ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀኑት የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከወላጅ ተነጥለው ለሳምንታት በነበራቸው ቆይታ ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች እና ተሞክሮዎች መነሻ በማድረግ አጠቃላይ የዳሰሳ ጥናት ተካሂዶ የተገኘው ውጤት ዋናውን የሀገር አቀፍ ፈተና አምሳያ(ሲሙሌሽን) አስቀድሞ ማዘጋጀት በእጅጉ አስፈለጊ እንደሆነ አመላክቷል፡፡
በ2014ዓ.ም የመጀመሪያው በዩኒቨርሲቲ የተካሄደው ብሄራዊ ፈተና ለተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ አንደመሆኑ ተማሪዎች ከወላጅ ተለይተው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በመግባት ፈተናዎችን የወሰዱበት ስለነበር በተማሪዎች መደናገጥን፣ስጋት እና አዲስ የአኗኗር ዘይቤን ለመልመድ የነበረው ትግል በራሱ ለፈተና ከሚኖረው ሰጋት ጋር ተዳምሮ ስጋት የፈጠረባቸውም እንደነበር ለመገንዘብ ችለናል፡፡
ይህንን የተማሪዎችን ሥነ-ልቦና እነ ሥነ-ባህሪ ላይ ዳሰሳ ያደረገው የኤስድሮስ ኤክስፐርቶች ቡድን በቀጣይ ምን ማድረግ ይገባል የሚል ጥቁምትን በመውሰድ በ2015 ዓ.ም ተፈታኝ ተማሪዎች ላይ በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት መነሻ እንደሆነም ታውቋል፡፡
ተማሪዎች በመማሪያ ክፍል ከየዕለት መማር ማስተማር ሂደት በተጨማሪ በተለይ ለ2015ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተና ዝግጀት በሥነ-ልቦናም ሆነ በፈተና ዝግጅት እንዲያደርጉ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ከትምህርት ዘርፍ ያገኘናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ለሀገር አቀፍ ፈተና ዝግጅት የ12ኛ፣ የ8ኛም ሆነ የ6ኛ ክፍል ተፈታኞች በሥነ-ልቦና እና በዕውቀት ዝግጁ ከማድረግ አንጻር የተለያዩ ሞዴል ፈተናዎችን የመሥራት ዕድል በመፍጠር በፈተና ሁለንተናዊ ዝግጅት ላይ ሊከተሉ የሚገቧቸውን መንገዶች የማሳየት ሥራዎች በሰፊው ተሠርተዋል፡፡
በተፈታኝ ተማሪዎች በኩል ትልቅ ልበ ሙልነት እና በራስ የመተማመን መፍጠር ካስቻሉ የሥነ-ልቦና ስልጠናዎች በተጨማሪ የቀጥታ ኢንተርኔት ፈተናዎችን በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች መሰጠቱ የበርካታ ጥያቄዎች ፈተና ሞዴል ፈተናዎችን ጥያቄዎችን መሥራት እና በርካታ ልምምዶችን እንዲያደርጉ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ ከነዚህ ልምምዶች በኋላም በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በአዳሪነት በመግባት የተሰጠው የዋናው ሀገር አቀፍ ፈተና አምሳያ (ሲሙሌሽን) የሞዴል ፈተና የማጠቃለያ መርሐግብር ነበር፡፡
ይህ የፈተና ሂደት ዋናውን ሀገር አቀፍ ፈተና እንዲመስል ፈተናዎችን በተለያየ ኮድ ከማዘጋጀት በተጨማሪ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩ መምህራን በፈታኝነት እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ ከፈተና ዝግጅት እስከ ፈተና አሰጣጥ ድረስም የተለያዩ ኤክስፐርቶች የተሳተፉበት እንዲሆን ተደርጓል፡፡

 

Abungorgorios