የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በታላቅ ድምቀት ተመረቁ

የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችን ተጋባዥ እንግዶች ፣ወላጆችና መምህራን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት አስመረቀ፡፡
ጦር ኃይሎች አካባቢ በሚገኘው መኮንኖች ክበብ አዳራሽ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም በተከናውነው የምረቃ መርሐግብር ላይ የኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ የዳሬክተሮች ቦርድ አባላት ፣የማኔጅመንት አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አንተነህ ፈለቀ በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው “እናንተ የዛሬ ተመራቂዎች የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች አምባሳደር ናችሁ፡፡ ለዚህ ያደረሳችሁን አምላክ፣ ወላጆቻችሁን እና መምህራኖቻችሁን ታመሰግኑ ዘንድ ይህ የምረቃ መርሐግብር ተዘጋጅቷል፡፡” የሚል መልክት ያስተላለፉ ሲሆን ለዝግጅቱ መሳካት አስተዋጽዖ ላደረጉ አካላት፣ ለኩባንያው የዳሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ ለማኔጅመንት አባላት፣ ለርዕሳነ መምህራን፣ ለመምህራን እና ለተማሪዎችን ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመርሀግሩም መምህር ዲ/ን ዮሐንስ ጌታቸው “መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ ያፈራል” በሚል የትምህርት ርዕስ “የዛሬ ተመራቂ ተማሪዎች ቀጣዩን የህይወት ምዕራፍ መልካምም ሆነ አስቸጋሪ ነገሮችን ለማለፍ ራሳችሁን ልታዘጋጁ ይገባል፡፡” በሚል ሰፊ ርዕሰ ጉዳዮች ከሕይወት ተሞክሯቸው ጋር በማመሳከር ልምድ ያካፈሉበት ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ዝግጀት የ2016 ዓ.ም በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች የአቧሬ፣የለቡ እና የሰሚት ተመራቂ ተማሪዎች በመወከል በዝግጅቱ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡ ተማሪ ሳሮን ሳሙኤል የአቧሬ ቅርንጫፍ ተመራቂ ተማሪዎችን በመወከል ንግግር ያደረገች ሲሆን “ከዕውቀታችሁ ሳትሰስቱ ያስተማራችሁን መምህራን ሆይ ስለተደረገልን ነገር ሁሉ እናመሰግናለን፡፡” የሚል መልዕክት አስተላልፋለች፡፡ የሰሚት ተመራቂ ተማሪዎችን በመወከል ተማሪ የማርያም ሰለሞን በመልዕክቷ “ቀሪው ህይወታችን የተሳካ እንዲሆን እንጸልይ፡፡” የሚል መልዕክት በማስተላለፍ ከታዳሚው ጋር ጸሎት አድርጋለች፡፡ የለቡ ቅርንጫፍ የተመራቂዎች ተወካይ የሆነው ተማሪ ያፌት ልሳነወርቅ በበኩሉ “በትምህርት ቤት ቆይታችን ስለማኅበረሰብ፣ሰለ ስኬትና ለእውነት የሚቆም ለፍትህ የሚታገል እንድንሆን አድርጋቹህ ቀርጻችሁናልና መምህራኖቻችን እናመሰግናለን፡፡” በማለት መልዕክት አስተላልፏል፡፡

በምረቃው ዝግጅትም ላይ በ2016 ዓ.ም ከ12ኛ ክፍል ተመራቂ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በዚህም ከአቧሬ ተማሪ ላዛሪ ከተፈጥሮ ሳይንስ እና ተማሪ ኤፍሬም ከማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ፤ ከለቡ ቅርንጫፍ ተማሪ ኃ/ሚካኤል ከተፈጥሮ ሳይንስ እና ተማሪ አዶናይ ከማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ፤ ከሰሚት ቅርንጫፍ ተማሪ ሳምሶን ከተፈጥሮ ሳይንስ እና ተማሪ ያፌት ከማኅበራዊ ሳይንስ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው ከኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ የዳሬክተሮች ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ከአቶ የሰውዘር በላይነህ የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በመርሐግብሩ ላይ ለተመራቂ ተማሪዎች ዲፕሎማና ስጦታዎችን ከኩባንያው የቦርድ አባላት እና የማኔጅመንት አካላት ተበርክቶላቸዋል፡፡


ለበለጠ መረጃ፡-
በስልክ ቁጥር 0930 363 779 በመደወል ወይም/እና የአክሲዮን ማኅበራችንን ድረ ገፅ https://esdros.com በመከታተል ወቅታዊ መረጃዎችን ያገኛሉ::