የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በይፋ ተከፈተ
የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መክፈቻ መርሐግብር ላይ ብጸዕ አቡነ ገሪማ፣ካህናት አባቶች፣ዲያቆናት፣ ወላጆች፣ተማሪዎች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም የትምህርት ኤክስፐርቶች በተገኙበት በደማቅ የመክፈቻ መርሐግብር ተከፈተ፡፡
በየትምህርት ቤቶቹ የተዘጋጀው የመክፈቻ መርሐግብር በብጸዕ አቡነ ገሪማ የጌድኦ፣አማሮ እና ቢርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣በካህናት አባቶች ጸሎተ ዕጣን እና ጸሎተ ወንጌል በማድረስ የተጀመረ ሲሆን የተለያዩ ዝግጅቶች ተከናውነዋል፡፡ በመርሐግብሩም የኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ መልዕክት ፣የቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር መልዕክት እና የወላጆች ተወካይ መልዕክት የተላለፈ ሲሆን መምህራን እና ተማሪዎች ዝማሬዎችን አቅርበዋል፡፡
በአቧሬ ቅርንጫፍ ተገኝተው ጸሎተ ወንጌል እና ቃለ ቡራኬ ያስተላለፉት የጌድኦ፣አማሮ እና ቢርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጸዕ አቡነ ገሪማ ”ወላጆች ለልጆቻችሁ ጊዜ ልትሰጡ ይገባል፡፡ የልጆቻችሁን ማኅበራ ሚዲያ አጠቃቀም ልትመሩት ይገባል፡፡ከአምላክ የተሠጣቹሁን የወላጅነት ድርሻ በአግባቡ መወጣት አለባቹህ፡፡ እናነተም ልጆች የወላጆቻችሁን ምክርና የሚያሳዩአችሁን መንገድ ልትከተሉ ይገባል ፡፡”በማለት አባታዊ ምክራቸውንና ቡራኬ አስተላልፈዋል፡፡
የ2017 ዓ.ም መስከረም 7 ቀን በተዘጋጀው የመክፈቻ መርሀግብር በየክፍላቸው ለተማሪዎች የትምህርት ቤቱን መመሪያ በማስተዋወቅ፣ በየክፍላቸው የጥናት ቡድን በመመስረት፣ እንደ ተሰጥኦ እና ፍላጎታቸው የተጓዳኝ ትምህርት (ክበብ) በመምረጥ፣ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሊያሳኩ የሚችሉትን የውጤት እቅድ በየትምህርት ዓይነቱ በማቀድ የትምህርት ዘመኑ በመጀመር የትምህርት ዘመኑ በይፋ መከፈቱን የሚያበስር የችቦ ቅብብል ተከናውኗል።
በዚህ መልክ የመክፈቻ መርሐግብር ያካሄዱት የአቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች ከመስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡
በተጠናቀቀው የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች በ6ኛ እና በ8ኛ ክፍል በከተማ እና በክልል በነበሩ ሚኒስትሪ ፈተናዎች 1ኛ በመውጣት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ሽልማት የተበረከተለት መሆኑ ይታወሳል፡፡ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመንም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ተጨማሪ ድሎችን ለማስመዝገብ ሙሉ ዝግጅት ማድረጉን ከመክፈቻ መርሐግብሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡