34ኛው ዝክረ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ መርሐግብር ተካሄደ

የሸዋ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ 34ኛ ዓመት መታሰቢያ መርሐግብር ተካሄደ፡፡ መርሐ ግብሩ የብፁታቸውን አስተምህሮ፣ስራዎቻቸውና ለሀገርና ለቤተክርስቲያን ያበረከቷቸውን ዘመን ተሸጋሪ አሻራዎች በመዘከር እና በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተዘክሮ ውሏል፡፡

መርሐ ግብሩ ለብፁነታቸው መታሰቢያ ትውልድን የሚተካ ትውልድ በተሻለ ጥራት ለማፍራት ታስቦ በስማቸው በተከፈቱት የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች በየቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ በመምህራን፣በክረምት ተማሪዎች እና አስተዳደር ሠራኞች እንዲሁም በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ ሰራተኞች በዋናው መስሪያ ቤት ታስቦ ውሏል፡፡
በመርሐግብሩም የብፁዕነታቸውን ሕይወት ከውልደት እስከ እረፍት የሚያወሳ ሥነ-ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን በዚህም በ1932ዓ.ም ከአቶ ገበየሁ እሰየና ከወ/ሮ አሰለፈች ካሣ በስእለት በደሴ ከተማ መወለዳቸው፣ በደሴ መድኃኔዓለም ፊደልን መቁጠር መጀመራቸው፣ በ1963ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት በብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ወደ ግሪክ መላካቸው፣በደሴተ ፍጥሞ ለሁለት ዓመት መንፈሳዊ ትምህርት ተምረው ዲፕሎማ፣ ከአቴንስ ዩኒቨርስቲ በሥነ መለኮት የማስትሬት ዲግሪ፣ ከስዊዘርላንድ ፍሪበሪን ዩኒቨርስቲ በፈረንሳይኛ ቋንቋ የምስክር ወረቀት እንዲሁም በኢየሩሳሌም ደብረ ጽዮን የግሪክ መንፈሳዊ ኮሌጅ- በአረብኛ ቋንቋ የምስክር ወረቀት ማግኘታቸው ተወስቷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ከተወሳው የብፁዕነታቸው ታሪክ አስገራሚው ሐምሌ 15 ቀን 1982 ዓ.ም. በሕጻናት አምባ (በዛሬው አላጌ ግብርና ኮሌጅ) የደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን መሠረት አስቀምጠው “ሰው የሚፈልገውን ከፈጸመ የሚጠብቀው ሞቱን ነው” በማለት ብዙዎችን የሚያስገርም ነገር ተናግረው ነበር፡፡

ብፁዕነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ የመተዳደሪያ ደንብ አዘጋጅተው እንዲጸድቅ ማድረግ የቻሉ ታላቅ ሊቅ ሲሆኑ ለካህናት ማሠልጠኛ ሥርዓተ ትምህርት ቀርጸው፡ የመማሪያና ማስተማሪያ ጥራዝ አዘጋጅተው ያስተምሩ ነበር፡፡ በዝዋይ ሐመረ ብርሃን በመሠረቱት የቅዱስ ገብርኤል ገዳም የዕውቀት ዓምባ አቋቁመው ኢትዮጵያዊውን ታሪክ ከዓለሙ ጋር እያነጻጸሩ ለደቀመዛሙርቶቻቸው ያስተመሩም ነበር። ለገዳማውያኑና ለትምህርት ከየከተማው ለሚሰባሰቡት ተማሪዎቻቸው ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ለተማሪዎቹ ዕውቀትና ሥነ ልቡና በሚመጥን መልኩ ሲያቀርቡ መስማት ያስደንቅ ነበር። ለትምህርት ወደ ዝዋይ የሚመጣ በበጀት እጥረት አይመለስም ነበር፡፡ በክረምት መኝታ ቤት ሞልቶ በድንኳን እያደሩ የሚማሩ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ብዙዎች ከዝዋይ መለየት አቅቷቸው በዚያው ቀርተዋል፡፡
የሃይማኖትና የታሪክ ጥናትና ምርምራቸውን “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” እና “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ” በሚሰኙ መጻሕፍቶቻቸው ቅልብጭ አድርገው አቅርበዋል።
በ1980 ዓ.ም. 12 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ተቀብለው በክረምት መርሐ ግብር ማስተማር የጀመሩት ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ለዛሬው የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበራት መስፋፋት መሠረት መጣላቸው በመርሐግብሩ ላይ ተወስቷል፡፡                                                                                                                                                                                                     

ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በነበሯቸው 10 የጵጵስና ዓመታት በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ለትውልድ መሠረት መጣል የቻሉ አባት እንደሆኑ በመርሐግብሩ ላይ ተወስቷል፡፡
ሐምሌ 22/1982 ዓ.ም በድንገተኛ የመኪና አደጋ በተወለዱ በሃምሳ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ሕይወታቸውን ያጡት ታሪክን እና የወንጌልን ብርሃን በወጣቱ ሕይወት ላይ ለመፈነጠቅ ወደ መቂ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት ሲፋጠኑ መሆኑን የታሪክ ድርሳናቸው ያወሳል፡፡
የብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ታሪካቸውን እምነታቸውንና ለሀገርና ለቤተክርስቲያን የነበራቸውን ራእይ ለትውልዱ እያሳወቀ አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶችን በመክፈትና በመሰየም ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ ዘወትር ብጹዕነታቸውን እየዘከራቸው ይገኛል፡፡